Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:54

[1] ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ።

[2] ምንአልባት በመንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵuራቦች የሥልጣን ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ ለመነ።

[3] ሲሄድም ወደ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ መብረቅ ድንገት ከሰማይ ብልጭ አለበት።

[4] በምድር ላይም ወደቀ፤ ወዲያውም ፥ “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ቃል ሰማ።

[5] ሳውልም ፥ “አቤቱ፥ አንተ ማነህ?” አለው፤ እርሱም ፥ “አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾለ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስሃል ” አለው።

[6] እርሱም እየፈራና እየተንቀጠቀጠ ፥ “አቤቱ፥ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?” አለው፤ ጌታም ፥ “ተነሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ይነግሩሃል ” አለው።

[7] ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ድምፅ እየሰሙ ማንንም ሳያዩ ተደንቀው ቆሙ።

[8] ሳውልም ከምድር ተነሣ፤ ነገር ግን ዐይኖቹ ተገልጠው ሳሉ የሚያየው ነገር አልነበረም፤ እየመሩም ወደ ደማስቆ አገቡት።

[9] በዚያም ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ቈየ።

[10] በደማስቆም ስሙን ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ ተገልጦ ፥ “ሐናንያ ” ብሎ ጠራው፤ እርሱም ፥ “አቤቱ፥ እነሆኝ ” አለ።

[11] ጌታም ፥ “ተነሣና ቅን በምትባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ከጠርሴስ ሀገር የመጣ ሳውል የሚባል ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን ይጸልያልና ” አለው።

[12] ሳውልም በራእይ ሐናንያ የሚባል ሰው ወደ እርሱ ገብቶ ያይ ዘንድ እጁን ሲጭንበት አየ።

[13] ሐናንያ ግን መልሶ እንዲህ አለ ፥ “አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው በኢየሩሳሌም በቅዱሳኖችህ ላይ የሚያደርገውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ።

[14] ወደዚህም ከካህናቱ አለቃ አስፈቅዶ የመጣ ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ሊያስር ነው።”

[15] ጌታችንም እንዲህ አለው ፥ “ተነሥና ሂድ፤ በአሕዛብና በነገሥታት፥ በእስራኤል ልጆችም ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና።

[16] እኔም ስለ ስሜ መከራን ይቀበል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ።”

[17] ያንጊዜም ሐናንያ ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ እጁንም ጫነበትና ፥ “ወንድሜ ሳውል፥ በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታይና መንፈስ ቅዱስ ይመላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል ” አለው።

[18] ያንጊዜም ፈጥኖ እንደ ቅርፊት ያለ ነገር ከዐይኖቹ ላይ ተገፎ ወደቀ፤ ዐይኖቹም ተገለጡ፤ ወዲያውም አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ።

[19] እህልም በላ፤ በረታም፤ ጥቂት ቀንም ከደቀ መዛሙርት ጋር በደማስቆ ሰነበተ።

[20] ወዲያውኑም “የእግዚአብሔር ልጅ ነው ” ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በየምኵuራቦቹ ሰበከ፥ አስተማረም።

[21] የሰሙትም ሁሉ አደነቁ፤ እንዲህም አሉ ፥ “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሁሉ ይጠላቸው የነበረው ይህ አይደለምን? ስለዚህ ወደዚህ የመጣው እያሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊወስዳቸው አይደለምን?”

[22] ሳውል ግን እየበረታ ሔደ፤ በደማስቆም ለነበሩት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ እያስረዳ መልስ አሳጣቸው።

[23] ከብዙ ቀንም በኋላ አይሁድ ሳውልን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ።

[24] ሳውል ግን በእርሱ ላይ ሊያደርጉት የሚሹትን ዐወቀባቸው፤ ሊገድሉትም በቀንና በሌሊት የከተማውን በር ይጠብቁ ነበር።

[25] ደቀ መዛሙርትም በሌሊት ወሰዱት፤ በቅርጫትም አድርገው በቅጽሩ ድምድማት ላይ አወረዱት።

[26] ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ሊገናኛቸው ደቀ መዛሙርትን ፈለጋቸው። ሁሉም ፈሩት፤ የጌታችን ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ አላመኑትም ነበርና።

[27] በርናባስም አግኝቶ ወደ ሐዋርያት ወሰደው፤ ጌታችንም በመንገድ እንደ ተገለጠለትና እንደ አነጋገረው፥ በደማስቆም በኢየሱስ ስም እንደ አስተማረ ነገራቸው።

[28] በኢየሩሳሌምም አብሮአቸው ይገባና ይወጣ ነበረ፤ በጌታችን በኢየሱስ ስምም በግልጥ ያስተምር ነበር።

[29] ከግሪክ ሀገር መጥተው የነበሩትንም አይሁድ ይከራከራቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ ሊገድሉት ፈለጉ።

[30] ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሳርያ አወረዱት፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ ላኩት።

[31] በይሁዳ፥ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ጸንተው ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ።

[32] ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ በየቦታዉ ሲዘዋወር በልዳ ወደሚኖሩት ቅዱሳን ዘንድ ደረሰ።

[33] በዚያም ኤንያ የተሰኘ ሰውን አገኘ፤ እርሱም ታሞ በአልጋ ከተኛ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ሽባ ነበርና።

[34] ጴጥሮስም ፥ “ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስህ፤ ተነሥና አልጋህን አንጥፍ ” አለው፤ ያንጊዜም ተነሣ።

[35] በልዳና በሳሮና የሚኖሩም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታችን ተመለሱ።

[36] በኢዮጴ ሀገርም ጣቢታ የምትባል አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ በትርጓሜውም ዶርቃስ ይሉአታል፤ ፌቆ ማለት ነው፤ እርስዋም ብዙ ደጋግ ሥራ ትሠራ ነበር፤ ምጿትም ትሰጥ ነበር።

[37] ያንጊዜም ታማ ሞተችና በድንዋን አጥበው በሰገነት አስተኙአት።

[38] ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ነበርና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው ወደ እነርሱ መምጣት እንዳይዘገይ ይማልዱት ዘንድ ሁለት ሰዎችን ወደ እርሱ ላኩ።

[39] ጴጥሮስም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በደረሰም ጊዜ ወደ ሰገነት አወጡት፤ ባልቴቶችም ሁሉ ወደ እርሱ መጥተው በፊቱ ቆሙ፤ ያለቅሱላትም ነበር፤ ዶርቃስም በሕይወት ሳለች የሠራችውን ቀሚሱንና መጐናጸፊያውን አሳዩት።

[40] ጴጥሮስም ሁሉን ካስወጣ በኋላ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ በድንዋም መለስ ብሎ ፥ “ጣቢታ ሆይ፥ ተነሽ ” አላት፤ እርስዋም ዐይኖችዋን ገለጠች፤ ያንጊዜም ጴጥሮስን አየችው፤ ቀና ብላም ተቀመጠች።

[41] እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና ባልቴቶችንም ጠርቶ እርስዋን አድኖ ሰጣቸው።

[42] በኢዮጴም ያሉ ሁሉ ይህን ሰሙ፤ ብዙዎችም በጌታችን አመኑ።

[43] ጴጥሮስም በኢዮጴ በቅWርበት ፋቂው በስምዖን ቤት ብዙ ቀን ተቀመጠ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters