[1] ሊቀ ካህናቱም ፥ “በእውነት እንዲህ ብለሃልን?” አለው።
[2] እርሱም እንዲህ አለ ፥ “ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ወደ ካራንም ሳይመጣ ተገለጠለት።
[3] ‘ካገርህ ውጣ፤ ከዘመዶችህም ተለይ፤ እኔም ወደማሳይህ ሀገር ና ’ አለው።
[4] ከዚህም በኋላ ከከለዳውያን ሀገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፤ ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ፥ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች ሀገር አመጣው።
[5] በውስጥዋም አንድ ጫማ ታህል ስንኳን ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን እርሱ ከእርሱም በኋላ ዘሩ ሊገዛት ልጅ ሳይኖረው ያንጊዜ እርስዋን ያወርሰው ዘንድ ተስፋ ሰጠው።
[6] እግዚአብሔርም እንዲህ አለው ፥ ‘ዘርህ በባዕድ ሀገር መጻተኟች ሆነው ይኖራሉ፤ አራት መቶ ዓመትም ባሮች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ መከራም ያጸኑባቸዋል።
[7] ደግሞም እግዚአብሔር አለ፤ ባሮች አድርገው በሚገዙአቸው ወገኖች እኔ እፈርድባቸዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ፤ በዚህም ሀገር ያመልኩኛል።’
[8] የግዝረትንም ኪዳን ሰጠው፤ ከዚህም በኋላ ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛው ቀንም ገረዘው፤ እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን፥ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የቀደሙ አባቶችን ገረዙ።
[9] “የቀደሙ አባቶችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብፅ ሀገር ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ።
[10] ከመከራውም ሁሉ አዳነው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፤ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይ ቢትወደድ አድርጎ ሾመው።
[11] በግብፅና በከነዓን ሀገር ሁሉ ረኃብና ታላቅ ጭንቅ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት አጡ።
[12] ያዕቆብም በግብፅ ሀገር እህል እንዳለ ሰማ፤ አባቶቻችንንም አስቀድሞ ላካቸው።
[13] ወደ ግብፅም እንደ ገና በተመለሱ ጊዜ ወንድሞቹ ዮሴፍን ዐወቁት፤ ፈርዖንም የዮሴፍን ዘመዶች ዐወቃቸው።
[14] ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ እንዲጠሩአቸው ላከ፤ ቐጥራቸውም ሰባ አምስት ነፍስ ነበር።
[15] “ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ፥ እርሱም አባቶቻችንም ሞቱ።
[16] ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በገንዘቡ በገዛው መቃብር ቀበሩዋቸው።
[17] “እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን በደረሰ ጊዜ እስራኤል በዙ፤ የግብፅንም ሀገር መሉ።
[18] ይህም ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ እስከ ነገሠ ድረስ ነበር።
[19] እርሱም ወገኖቻችንን ተተንኵuሎ አባቶቻችንን መከራ አጸናባቸው፤ ወንድ ልጅንም ሁሉ እንዲገድሉ አዘዘ።
[20] “ያንጊዜም ሙሴ ተወለደ፤ በእግዚአብሔር ፊትም የተወደደ ሆነ፤ ለሦስት ወርም በአባቱ ቤት አሳደጉት።
[21] በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው፤ ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው።
[22] ሙሴም የግብፅን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በሚናገረውና በሚሠራውም ሁሉ ብርቱ ሆነ።
[23] “አርባ ዓመት ሲሞላውም ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኛቸው በልቡ ዐሰበ።
[24] አንድ ግብፃዊም ዕብራዊውን ሲበድለው አገኘና ለዚያ ለተበደለው ረድቶ ግብፃዊውን ገደለው በአሸዋም ቀበረው።
[25] እርሱም እግዚአብሔር በእጁ ድኅነትን እንደሚያደርግላቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
[26] በማግሥቱም ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኘ፤ ሊያስታርቃቸውም ወድዶ ፥ ‘እናንተማ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ለምን ትጣላላችሁ?’ አላቸው።
[27] ያም ባልንጀራውን የሚበድለው ገፋው፤ እንዲህም አለው ፥ ‘አንተን በእኛ ላይ ዳኛና ፈራጅ አድርጎ ማን ሾመህ?
[28] ወይስ ትናንትና ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትሻለህን?’
[29] ስለዚህም ነገር ሙሴ ኮብልሎ በምድያም ሀገር ስደተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆችን ወለደ።
[30] “አርባ ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ በበረሃ በደብረ ሲና የእግዚአብሔር መልአክ በቅWጥቌጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው።
[31] ሙሴም አይቶ በአየው ተደነቀ፤ ሊያስተውለውም ቀረበ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው።
[32] ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤’ ሙሴም ተንቀጠቀጠ፤ መረዳትም አልቻለም።
[33] እግዚአብሔርም እንዲህ አለው ፥ ‘ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤ የቆምህባት ምድር የተቀደሰች ናትና።
[34] በግብፅ ያሉትን የወገኖቼን መከራ ማየትን አይቻለሁ፤ ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ፤ አሁንም ና ወደ ግብፅ ሀገር ልላክህ።’
[35] “በእኛ ላይ አለቃና ፈራጅ ማን አድርጎሃል? ብለው የካዱትን ያን ሙሴን በቅWጥቌጦው መካከል በታየው በመልአኩ እጅ እርሱን መልእክተኛና አዳኝ አድርጎ እግዚአብሔር ላከው።
[36] እርሱም አርባ ዘመን በግብፅ ሀገርና በኤርትራ ባሕር፥ በበረሃም ተአምራትንና ድንቅ ሥራን እየሠራ አወጣቸው።
[37] ለእስራኤልም ልጆች ፥ ‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና እርሱን ስሙት ’ ያላቸው ይህ ሙሴ ነው።
[38] በምድረ በዳ በማኅበሩ መካከል የነበረ እርሱ ነው፤ በደብረ ሲና ከአነጋገረው መልአክና፤ ከአባቶቻችንም ጋር ለእኛ ሊሰጠን የሕይወትን ቃል የተቀበለ እርሱ ነው።
[39] አባቶቻችን ለእርሱ መታዘዝን እንቢ አሉ፤ ከዱትም፤ ልባቸውንም ወደ ግብፅ ሀገር መለሱ።
[40] አሮንንም ፥ ‘በፊት በፊታችን የሚሄዱ አማልክትን ሥራልን፤ ያ ከምድረ ግብፅ ያወጣን ሙሴ የሆነውን አናውቅምና ’ አሉት።
[41] ያንጊዜም የጥጃ ምስል ሠሩ፤ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸው ሥራም ደስ አላቸው።
[42] እግዚአብሔርም ተለያቸው፤ የሰማይ ጭፍራን ያመልኩም ዘንድ ተዋቸው፤ የነቢያት መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ፤ ‘እናንት የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ ሳላችሁ አርባ ዐመት ያቀረባችሁልኝ ቅWርባንና መሥዋዕት አለን?
[43] ነገር ግን የሞሎህን ድንኳን አነሣችሁ፤ ሬፋን የሚባለውንም ኮከብ አመለካችሁ፤ ትሰግዱላቸውም ዘንድ ምስሎቻቸውን አበጃችሁ፤ እኔም ወደ ባቢሎን እንድትማረኩ አደርጋችኋለሁ።’
[44] “ሙሴን ተናግሮ እንደ አዘዘው በአሳየው ምሳሌ የሠራት የምስክር ድንኳን በአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች።
[45] ኢያሱና አባቶቻችንም በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ፊት አስወጥቶ ወደ ሰደዳቸው ወደ አሕዛብ ሀገር ከእነርሱ ጋር አገቡአት፤ እስከ ዳዊት ዘመንም ነበረች።
[46] ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ባለመዋልነትን አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያገኝ ዘንድ ለመነ።
[47] ሰሎሞን ግን ቤትን ሠራለት።
[48] ነገር ግን ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት የሚኖር አይደለም፤ ነቢይ እንዲህ ብሎአልና።
[49] እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ፥ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበት ቦታስ ምን ዐይነት ቦታ ነው?
[50] ይህን ሁሉ እጆቼ የሠሩት አይደለምን?’
[51] “እናንተ አንገታችሁ የደነደነ፥ ልባችሁም የተደፈነ፥ ጆሮአችሁም የደነቈረ፥ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ትቃወማላችሁ።
[52] አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ማን አለ? ዛሬም እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና የገደላችሁትን የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው።
[53] በመላእክትም ሥርዐት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁትም።”
[54] ይህንም ሰምተው ተበሳጩ፤ ልባቸውም ተናደደ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።
[55] በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላ፤ ወደ ሰማይም ተመለከተ፤ የእግዚአብሔርን ክብር፥ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ።
[56] “እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፤ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ ” አለ።
[57] እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፈኑ፤ በአንድነትም ተነሥተው ከበቡት።
[58] ከከተማም ወደ ውጭ ጐትተው አውጥተው ወገሩት፤ የሚወግሩት ሰዎችም ልብሳቸውን ሳውል በሚባል ጐልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።
[59] እስጢፋኖስም ፥ “ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ” እያለ ሲጸልይ ይወግሩት ነበር።
[60] በጕuልበቱም ተንበርክኮ ፥ “አቤቱ፥ ይህን ኀጢአት አትቅWጠርባቸው ” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ ሞተ፤ ሳውልም በእስጢፋኖስ ሞት ተባባሪ ነበር።