Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:40

[1] ጳውሎስም በአደባባዩ ወደአሉት ሰዎች አተኵuሮ ተመለከተና ፥ “እናንተ ሰዎች ወንድሞቼ፥ እኔስ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ እግዚአብሔርን ሳገለግል ኑሬአለሁ ” አላቸው።

[2] ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ግን ጳውሎስን አፉን እንዲመቱት በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ።

[3] ጳውሎስም መልሶ ፥ “አንተ የተለሰነ ግድግዳ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዝዛለህን? እግዚአብሔር በቐጣው መቅሠፍት ይመታሃል ” አለው።

[4] በአጠገቡ ቆመው የነበሩትም ጳውሎስን ፥ “እግዚአብሔር የሾመውን ሊቀ ካህናት እንዴት ትሳደባለህ?” አሉት።

[5] ጳውሎስም ፥ “ወንድሞቼ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላውቅም መጽሐፍ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር ’ ይላልና ” አላቸው።

[6] ጳውሎስም እኩሌቶቹ ሰዱቃውያን እኩሌቶቹም ፈሪሳውያን እንደ ሆኑ ዐውቆ ፥ “እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊ ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣትም ይፈረድብኛል ” ብሎ በአደባባይ ጮኸ።

[7] እንዲህም ባለ ጊዜ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ተጣሉ፤ ሸንጎውም ተከፋፈለ።

[8] ሰዱቃውያን ፥ “ሙታን አይነሡም፤ መልአክም የለም፤ መንፈስም የለም ” ይላሉና፤ ፈሪሳውያን ግን ይህ ሁሉ እንዳለ ያምናሉ።

[9] ታላቅ ውካታም ሆነ፤ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑ ጸሐፍት ተነሥተው ይጣሉና ይከራከሩ ጀመሩ፤ “በዚህ ሰው ላይ ያገኘነው ክፉ ነገር የለም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮት እንደ ሆነ እንጃ፥ ከእግዚአብሔር ጋር አንጣላ ” አሉ።

[10] እጅግም በታወኩ ጊዜ ጳውሎስን እንዳይነጥቁት የሻለቃው ፈራና መጥተው ከመካከላቸው አውጥተው ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ።

[11] በሁለተኛዪቱም ሌሊት ጌታችን ለጳውሎስ ተገልጦ ፥ “ጽና፥ በኢየሩሳሌም ምስክር እንደ ሆንኸኝ እንዲሁ በሮም ምስክር ትሆነኛለህ ” አለው።

[12] በነጋም ጊዜ አይሁድ ተሰብስበው፥ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተስማምተው ተማማሉ።

[13] ይህንም ለማድረግ የተማማሉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር።

[14] እነርሱም ወደ ሊቃነ ካህናትና ወደ መምህራን ሄደው እንዲህ አሉአቸው ፥ “ጳውሎስን እስክንገድለው ድረስ እነሆ፥ እንዳንበላና እንዳንጠጣ ፈጽመን ተማምለናል።

[15] አሁንም እናንተ ከሸንጎው ጋር ወደ ሻለቃው ሂዱና የምትመረምሩትና የምትጠይቁት አስመስላችሁ ጳውሎስን እንዲያመጣው ንገሩት፤ እኛ ግን ወደ እናንተ ከመድረሱ አስቀድሞ ልንገድለው ቈርጠናል።”

[16] የጳውሎስም የእኅቱ ልጅ ምክራቸውን በሰማ ጊዜ ሄዶ ወደ ወታደሮች ሰፈር ገባና ለጳውሎስ ነገረው።

[17] ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ ፥ “የሚነግረው ነገር አለና ይህን ልጅ ወደ የሻለቃው አድርስልኝ ” አለው።

[18] የመቶ አለቃውም ልጁን ይዞ ወደ የሻለቃው ወሰደውና ፥ “የሚነግርህ ስለ አለው እስረኛው ጳውሎስ ይህን ልጅ ወደ አንተ እንዳደርሰው ለመነኝ ” አለው።

[19] የሻለቃውም ልጁን በእጁ ይዞ ለብቻው ገለል አድርጎ ፥ “የምትነግረኝ ነገሩ ምንድነው?” አለው።

[20] ልጁም እንዲህ አለው ፥ “አይሁድ አጥብቀህ የምትመረምረው መስለህ ጳውሎስን ነገ ወደ ሸንጎ ታወርድላቸው ዘንድ ሊማልዱህ እንዲህ መክረዋል።

[21] አንተ ግን እሽ አትበላቸው፤ ሊገድሉት ሽምቀዋልና፤ እስኪገድሉትም ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ እንዲህ የተማማሉ ሰዎች ከአርባ ይበዛሉ፤ አሁንም እስክትልክላቸው ይጠብቃሉ እንጂ እነርሱ ቈርጠዋል።”

[22] ከዚህም በኋላ፤ የሻለቃው ፥ “ይህን ነገር ለእኔ መንገርህን ለማንም እንዳትገልጽ ” ብሎ አሰናበተው።

[23] ከመቶ አለቆችም ሁለቱን ጠርቶ ፥ “ከወታደሮች ሁለት መቶ ሰውና ሰባ ፈረሰኟች፥ ሁለት መቶ ቀስተኟችም ምረጡ፤ ከሌሊቱም በሦስት ሰዓት ወደ ቂሣርያ ይሂዱ ” አላቸው።

[24] አህያም አምጥተው ጳውሎስን በዚያ አስቀምጠው ወደ ቂሣርያ አገረ ገዢ ወደ ፊልክስ እንዲወስዱት አዘዛቸው።

[25] እንዲህ የምትል ደብዳቤም ጻፈለት።

[26] “ከሉስዮስ ቀላውዴዎስ፥ ለክቡር አገረ ገዢ ፊልክስ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን።

[27] ይህን ሰው አይሁድ ያዙት፤ ሊገድሉትም ፈለጉ፤ ከወታደሮቼም ጋር ተከላከልሁለት፥ የሮም ሰው መሆኑንም ዐውቄ አዳንሁት።

[28] በምን ምክንያትም እንደሚከሱት በደሉን አውቅ ዘንድ ወደ ሸንጎ አቅርቤ መረመርሁት።

[29] ስለ ሕጋቸውም ብቻ እንደ ከሰሱት ተረዳሁ፤ ለሞትና ለመታሰር የሚያበቃ ሌላ በደል ግን የለበትም።

[30] አይሁድም በዚህ ሰው ላይ በመሸመቅ የሚያደርጉትን በዐወቅሁ ጊዜ ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹንም ወደ አንተ እንዲመጡና በፊትህ እንዲፋረዱት አዝዣቸዋለሁ፤ ደኅና ሁን።”

[31] ጭፍሮችም እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ጳውሎስንም በሌሊት ወሰዱት፤ ወደ አንቲጳጥሪስም አደረሱት።

[32] በማግሥቱም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኟችን ትተው እነርሱ ወደ ሰፈር ተመለሱ።

[33] ከዚህም በኋላ ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ወደ አገረ ገዢውም ደረሱ፤ የተላከውንም ደብዳቤ ለአገረ ገዢው ሰጡት፤ ጳውሎስንም ወደ እርሱ አቀረቡት።

[34] ደብዳቤውንም ካነበበ በኋላ ከማን ግዛት እንደ ሆነ ጠየቀው። ከኪልቅያ የመጣ መሆኑንም ባወቀ ጊዜ ፥

[35] “እንኪያስ ከሳሾችህ ሲመጡ እንሰማሃለን ” አለው፤ በሄሮድስም ግቢ እንዲጠብቁት አዘዘ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters