[1] በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር።
[2] እርሱም ጻድቅና ከነቤተ ሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጿት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር።
[3] የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ ፥ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥” አለው።
[4] ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና ፥ “አቤቱ፥ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው ፥ “ጸሎትህም ምጿትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል።
[5] አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ።
[6] እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቅWርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል። ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።”
[7] ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት፥ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ።
[8] ነገሩንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካቸው።
[9] በማግሥቱም ሄደው ወደ ከተማዪቱ በር ደረሱ፤ ጴጥሮስም በቀትር ጊዜ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጥቶ ነበር።
[10] በተራበ ጊዜም ምሳ ሊበላ ወደደ፤ እነርሱም እያዘጋጁ ሳሉ ተመስጦ መጣበት።
[11] ሰማይም ተከፍቶ በአራቱ ማዕዘን የተያዘ እንደ ታላቅ መጋረጃ ያለ ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ።
[12] በውስጡም አራት እግር ያለው እንስሳ ሁሉ፥ አራዊትም፥ የሚንቀሳቀስም፥ የሰማይም ወፎች ነበሩበት።
[13] “ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ።
[14] ጴጥሮስ ግን ፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ርኩስ፥ የሚያጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅም ” አለው።
[15] ዳግመኛም ፥ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክስ ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ።
[16] ይህንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲያውኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመለሰ።
[17] ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር።
[18] ተጣርተውም ፥ ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ።
[19] ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው ፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል።
[20] ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና።”
[21] ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና ፥ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው።
[22] እነርሱም ፥ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ በአይሁድም ወገኖች ሁሉ የተመሰከረለት ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት።
[23] እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ።
[24] በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር።
[25] ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት።
[26] ጴጥሮስም ፥ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ ” ብሎ አነሣው።
[27] ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ።
[28] ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው ፥ “ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ።
[29] አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ።”
[30] ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው ፥ “የዛሬ አራት ቀን በዘጠኝ ሰዓት በዚች ሰዓት በቤቴ ስጸልይ የሚያንፀባርቅ ልብስ የለበሰ አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ ታየኝ።
[31] እንዲህም አለኝ ፥ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ፤ ምጿትህም ታሰበልህ።
[32] አሁንም ወደ ኢዮጴ ከተማ ላክና በባሕር አቅራቢያ ባለችው በቐርበት ፋቂው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ፤ እርሱ መጥቶ የምትድንበትን ይነግርሃል።
[33] ስለዚህም ወዲያውኑ ወደ አንተ ላክሁ፤ ወደ እኛ በመምጣትህም መልካም አደረግህ፤ አሁንም እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ ልንሰማ እነሆ፥ እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።”
[34] ጴጥሮስም አፉን ከፈተና እንዲህ አለ ፥ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላ በእውነት አየሁ።
[35] ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ እርሱን የሚፈራና እውነትን የሚያደርግ በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።
[36] ቃሉን ለእስራኤል ልጆች ላከ፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምን ነገራቸው፤ እርሱም የሁሉ ገዢ ነው።
[37] ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ የሆነውን ነገር ሁሉ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
[38] ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው፥ እየዞረም መልካም እንደ አደረገ፥ ሰይጣን ያሸነፋቸውንም እንደ ፈወሰ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና።
[39] በይሁዳና በኢየሩሳሌም ባደረገውም ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።
[40] እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ በግልጥ እንዲታይም አደረገው።
[41] ይኸውም ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን አስቀድሞ ለመረጣቸውና ምስክሮች ለሚሆኑት ብቻ ነው እንጂ፤ የመረጣቸው የተባልንም እኛ ነን፤ ከሙታንም ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።
[42] በእግዚአብሔር ዘንድ በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ ሆኖ የተሾመ እርሱ እንደ ሆነ ለሕዝብ እናስተምር ዘንድ አዘዘን።
[43] ለሚያምኑበትም ሁሉ ኀጢአታቸው በስሙ እንደሚሰረይላቸው ነቢያት ሁሉ ምስክሮቹ ናቸው።”
[44] ጴጥሮስም ይህን ነገር ሲነግራቸው ይህን ትምህርት በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።
[45] ከጴጥሮስ ጋር የመጡ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ምእመናን ሁሉ ደነገጡ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በአሕዝብ ላይ ወርዶአልና።
[46] በልዩ ልዩ ሀገር ቌንቌ ሲናገሩ፥ እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ ሰምተዋቸዋልና።
[47] ጴጥሮስም ፥ “እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እንግዲህ በውኃ እንዳይጠመቁ ውኃን ሊከለክላቸው የሚችል ማነው?” አለ።
[48] በኢየሱስ ክርስቶስም ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ጥቂት ቀን አብሮአቸው እንዲቀመጥ ጴጥሮስን ማለዱት።