Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:38

[1] በዚያም ወራት ደቀ መዛሙርት በበዙ ጊዜ ከግሪክ የመጡ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ ምእመናን ላይ አንጐራጐሩባቸው፤ የዕለት የዕለቱን ምግብ ሲያካፍሉ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ነበርና።

[2] ዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሉአቸው ፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም።

[3] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን።

[4] እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።”

[5] ይህም ነገር በእነርሱ ዘንድ የተወደደ ሆነ፤ ሃይማኖቱ የቀናና መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን ሰው እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስን፥ ጵሮኮሮስን፥ ኒቃሮናን፥ ጢሞናን፥ ጰርሜናን፥ ወደ ይሁዲነት የተመለሰውን የአንጿኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ።

[6] በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፤ ጸልየውም እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጫኑ።

[7] የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ ከፍ አለ፤ በኢየሩሳሌምም ምእመናን እጅግ በዙ፤ ከካህናትም መካከል ያመኑ ብዙዎች ነበሩ።

[8] እስጢፋኖስም የእግዚአብሔር ጸጋና ኀይል የመላበት ሰው ነበር፤ በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ ነበር።

[9] የነጻ ወጭዎች ከምትባለው ምኵuራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያ፥ ከቂልቅያና ከእስያ የሆኑ ሰዎችም ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር።

[10] ነገር ግን ይቃወሙት ዘንድ አልቻሉም፤ በጥበብና በመንፈስ ቅዱስ ይከራከራቸው ነበርና።

[11] ከዚህም በኋላ “ይህን ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል ” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አስነሡበት፤

[12] ሕዝቡን፥ ሽማግሌዎችንና ጸሓፊዎችንም አነሳሡአቸው፤ ከበውም እየጐተቱ ወደ ሸንጎ አቀረቡት።

[13] የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት፤ እነርሱም እንዲህ አሉ ፥ “ይህ ሰው በዚህ ቤተ መቅደስ ላይና በኦሪት ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ ዝም በል ቢሉት እንቢ አለ፤

[14] የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ቤተ መቅደስ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም የሰጠንን ኦሪታችንን ይሽራል ሲል ሰምተነዋል።”

[15] በሸንጎም ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ተመለከቱት፤ ፊቱንም እንደ እግዚአብሔር መልአክ ፊት ሆኖ አዩት።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters