[1] ፊስጦስም ወደ ቂሣርያ ደርሶ ሦስት ቀን ሰነበተ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
[2] ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሎችም ከበቡት፤ የጳውሎስንም ነገር ነገሩት።
[3] ልኮም ወደ ኢየሩሳሌም አደባባይ እንዲያስመጣውና እንዲሰጣቸው ለመኑት፤ እነርሱ ግን ወደዚያ ሄደው በመንገድ ሸምቀው ሊገድሉት ፈልገው ነበር።
[4] ፊስጦስም ጳውሎስን በቂሣርያ እንደሚጠብቁት፥ እርሱም ራሱ ወደዚያው በቶሎ እንደሚሄድ መለሰላቸው።
[5] አይሁድንም ፥ “ከመካከላችሁ የሚችሉ ካሉ ከከሰሳችሁት ከዚያ ሰው ጋር እንዲከራከሩ ከእኔ ጋር ይውረዱ ” አላቸው።
[6] ስምንት ወይም ዐሥር ቀን በእነርሱ ዘንድ ከሰነበተ በኋላ ወደ ቂሣርያ ሄደ፤ በማግሥቱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ።
[7] ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱ አይሁድ ከብበውት ቆሙ፤ ሊረቱ በማይችሉበትም ብዙና ከባድ ክስ ከሰሱት።
[8] ጳውሎስም ሲመልስ ፥ “በአይሁድ ሕግ ላይ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ላይ ቢሆን፥ በቄሣር ላይም ቢሆን አንዳች የበደልሁት የለም ” አለ።
[9] ፊስጦስ ግን አይሁድ እንዲያመሰግኑት ወዶ ጳውሎስን ፥ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር በዚያ ከእኔ ዘንድ ልትከራከር ትሻለህን?” አለው።
[10] ጳውሎስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ ወደ ቄሣር ዙፋን ችሎት እቀርባለሁ፤ ፍርዴም በዚያ ሊታይልኝ ይገባል፤ በአይሁድም ላይ የበደልሁት በደል እንደሌለኝ ከሰው ሁሉ ይልቅ አንተ ራስህ ታውቃለህ።
[11] ከበደልሁ ወይም ለሞት የሚያበቃኝ የሠራሁት ክፉ ሥራ ካለ ሞት አይፈረድብኝ አልልም፤ ነገር ግን እነዚህ በደል የሌለብኝን በከንቱ የሚከስሱኝ ከሆነ፥ ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጠኝ ለማን ይቻለዋል? እኔ ወደ ቄሣር ይግባኝ ብያለሁ።”
[12] ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ ፥ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ካልህ ወደ ቄሣር ትሄዳለህ ” አለው።
[13] ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት።
[14] በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው ፥ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ።
[15] በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ።
[16] እኔም ፥ ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም፥ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው።
[17] ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ፥ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ።
[18] የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ፥ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም።
[19] ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው፥ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤
[20] ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት።
[21] ጳውሎስ ግን እንቢ ብሎ፥ እንዲድን ወደ ቄሣር ይግባኝ አለ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቄሣር እስክልከው ድረስ እንዲጠብቁት አዘዝሁ።”
[22] አግሪጳም ፊስጦስን ፥ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወዳለሁ ” አለው፤ ፊስጦስም ፥ “እንግዲያስ ነገ ትሰማዋለህ ” አለው።
[23] በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ።
[24] ፊስጦስም እንዲህ አለ ፥ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ፥ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ።
[25] እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ፥ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ።
[26] ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም። ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት።
[27] የበደሉ ደብዳቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል።”