[1] በዚያም ወራት ሄሮድስ የቤተ ክርስቲያንን ሹሞች ያዛቸው፤ መከራም አጸናባቸው።
[2] የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው።
[3] አይሁድንም ደስ እንዳላቸው አይቶ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው፤ ያንጊዜም የፋሲካ በዓል ነበር።
[4] ይዞም ወኅኒ ቤት አስገባው፤ ለሚጠብቁት ለዐሥራ ስድስቱ ወታደሮችም አሳልፎ ሰጠው፤ ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ሊያቀርበው ወድዶ ነበር።
[5] ጴጥሮስንም በወኅኒ ቤት ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ ክርስቲያንም ዘወትር ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር።
[6] ሄሮድስም ማለዳ ያቀርበው ዘንድ በወደደባት በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ ሁለቱን እጆቹን በሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም የወኅኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር።
[7] የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ በአጠገቡ ቆመ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን ሆነ፤ ጴጥሮስንም ጎኑን ነክቶ ቀሰቀሰውና ፥ “ፈጥነህ ተነሥ ” አለው፥ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ወልቀው ወደቁ።
[8] መልአኩም ፥ “ወገብህን ታጠቅ፥ ጫማህንም ተጫማ ” አለው፤ እንደ አዘዘውም አደረገ፤ “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ ” አለው።
[9] ተከትሎትም ወጣ፤ ጴጥሮስ ግን ራእይ የሚያይ ይመስለው ነበረ እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም ነበር።
[10] መጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደምትወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ ያንጊዜም መዝጊያው ራሱ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም በአንድ ስላች መንገድ ሄዱ፤ መልአኩም ጴጥሮስን ትቶት ሄደ።
[11] ያንጊዜም የጴጥሮስ ልቡና ተመለሰለትና ፥ “እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ በእውነት አሁን ዐወቅሁ ” አለ።
[12] ከዚህም በኋላ በአስተዋለ ጊዜ ብዙዎች ወንድሞች ተሰብስበው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ።
[13] ጴጥሮስም በሩን አንኳኳ፤ ሮዴ የምትባል ብላቴናም ልትከፍትለት መጣች።
[14] የጴጥሮስም ድምፅ መሆኑን ዐውቃ ከደስታ የተነሣ አልከፈተችለትም፤ ነገር ግን ጴጥሮስ በበር ቆሞ ሳለ ሮጣ ነገረቻቸው።
[15] እነርሱም “አብደሻልን? አንድ ጊዜ ታገሺ ” አሉአት፤ እርስዋ ግን እርሱ እንደ ሆነ ታረጋግጥ ነበር። እነርሱም ፥ “ምናልባት መልአኩ ይሆናል ” አሉ።
[16] ጴጥሮስ ግን በሩን ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ ከፍተውም ባዩት ጊዜ ተደነቁ።
[17] እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመለከታቸው፤ ከወኅኒ ቤትም እግዚአብሔር እንደ አወጣው ነገራቸው፤ “ይህንም ለያዕቆብና ለወንድሞች ሁሉ ንገሩ ” አላቸው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።
[18] በነጋ ጊዜም ወታደሮች ፥ “ጴጥሮስ ምን ሆነ?” ብለው ታወኩ።
[19] ሄሮድስ ግን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ፤ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
[20] ሄሮድስም በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ተቈጥቶ ነበር፤ በአንድነትም ወደ እርሱ መጥተው የንጉሡን ቢትወደድ በላስጦስን እንዲያስታርቃቸው ማለዱት፤ የሀገራቸው ምግብ ከንጉሥ ሄርድስ ነበርና።
[21] ከዚህም በኋላ አንድ ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ፥ በአደባባይ ተገኝቶ ይፈርድ ጀመረ።
[22] ሕዝቡም ፥ “የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የሰው ቃልም አይደለም ” እያሉ ጮኹ።
[23] ለእግዚአብሔርም ክብር ስለ አልሰጠ ያንጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቀሠፈው፤ ተልቶም ሞተ።
[24] የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ አለ፤ በዛም።
[25] በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም አስከትለውት መጡ።