[1] “እናንተ ወንድሞችና አባቶች፥ አሁን በፊታችሁ የምናገረውን ስሙኝ።”
[2] በዕብራይስጥ ቌንቌ እንደሚነግራቸው በሰሙም ጊዜ ጸጥ ብለው አዳመጡት።
[3] ጳውሎስም እንዲህ አላቸው ፥ “እኔ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የቂልቅያ ክፍል በምትሆን በጠርሴስ ከተማ ተወለድሁ፤ በዚችም ከተማ ከገማልያል እግር ሥር ሆኜ አደግሁ፤ የአባቶቼንም ሕግ ተማርሁ፤ እናንተ ሁላችሁ ዛሬ እንደምታደርጉትም ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ነበርሁ።
[4] ይህን ትምህርት የሚከተሉ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት እስከ ሞት ድረስ አሳደድኋቸው።
[5] እንዲቀጡም ከዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ወደ አሉ ወንድሞች እንድሄድ ከእነርሱ ዘንድ የሥልጣን ደብዳቤ የተቀበልኋቸው ሊቀ ካህናቱና መምህራን ሁሉ ይመሰክራሉ።
[6] “ከዚህ በኋላ ወደ ደማስቆ ስሄድ ቀትር በሆነ ጊዜ ወደ ከተማው አቅራቢያ ደርሼ ሳለሁ ድንገት ታላቅ መብረቅ ከሰማይ በእኔ ላይ አንፀባረቀ።
[7] በምድር ላይም ወደቅሁ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ቃልንም ሰማሁ።
[8] እኔም መልሼ ፥ ‘አቤቱ፥ አንተ ማነህ?’ አልሁት፤ እርሱም ፥ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ ’ አለኝ።
[9] አብረውኝ የነበሩትም መብረቁን አይተው ደነገጡ፤ ነገር ግን ይናገረኝ የነበረውን ቃል አልሰሙም።
[10] ‘አቤቱ፥ ጌታዬ ምን ላድርግ?’ አልሁ፤ ጌታም ፥ ‘ተነሥና ወደ ደማስቆ ሂድ፤ ልታደርገው የሚገባህንም ሁሉ በዚያ ይነግሩሃል ’ አለኝ።
[11] ከዚያም በኋላ ከመብረቁ ነፀብራቅ የተነሣ ዐይኔን ታወርሁ፤ አብረውኝ የነበሩትም እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ።
[12] “እንደ ሕጉም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በደማስቆም የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ያመሰግኑት ነበር።
[13] ወደ እኔም መጥቶ በፊቴ ቆመና ፥ ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ ’ አለ፤ ያንጊዜም ወደ እርሱ አየሁ።
[14] እንዲህም አለኝ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅና ጽድቁንም ታይ ዘንድ፥ ቃሉንም ከአንደበቱ ትሰማ ዘንድ መረጠህ።
[15] በሕዝብም ሁሉ ዘንድ ባየኸውና በሰማኸው ምስክር ትሆነዋለህ።
[16] አሁንም የምታደርገውን ልንገርህ ፥ ተነሥ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’
[17] “ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ በቤተ መቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ።
[18] ‘ስለ እኔ የምትመሰክረውን ምስክርነት አይቀበሉህምና ከኢየሩሳሌም ፈጥነህ ውጣ ’ ሲለኝ አየሁት።
[19] እኔም እንዲህ አልሁት ፥ ‘ጌታዬ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በየምኵuራቦቻቸው ሳስራቸውና ስደበድባቸው የነበርሁ እኔ እንደ ሆንሁ እነርሱ ያውቃሉ።
[20] ሰማዕትህን እስጢፋኖስን በገደሉትም ጊዜ እኔ እዚያ አብሬአቸው ነበርሁ፤ የገዳዮችንም ልብስ እጠብቅ ነበር።’
[21] እርሱም ፥ ‘ሂድ ርቀው ወደ አሉ አሕዛብ እልክሃለሁና ’ ” አለኝ።
[22] ከጳውሎስም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ “ይህ በሕይወት ሊኖር አይገባውምና እንዲህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው ” እያሉ ጮሁ።
[23] እነርሱም እየጮሁና ልብሳቸውንም እየወረወሩ ትቢያውን ወደ ላይ ሲበትኑ፥
[24] የሻለቃው የሚጮሁበት ስለ ምን እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ወደ ወታደሮች ሰፈር እንዲያገቡትና እየገረፉ የሠራውን እንዲመረምሩት አዘዘ።
[25] ሊገርፉትም በአጋደሙት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የነበረውን የመቶ አለቃ ፥ “የሮማን ሰው ያለ ፍርድ ልትገርፉ ይገባችኋልን?” አለው።
[26] የመቶ አለቃውም ይህን በሰማ ጊዜ፥ ወደ ሻለቃው ሄደና ፥ “ይህ ሰው ሮማዊ ነው፥ የምታደርገውን ዕወቅ ” ብሎ ነገረው።
[27] የሻለቃውም ወደ እርሱ ቀርቦ ፥ “አንተ ሮማዊ ነህን? እስኪ ንገረኝ ” አለው፤ ጳውሎስም ፥ “አዎን ” አለው።
[28] የሻለቃውም መልሶ ፥ “እኔ ይህችን ዜግነት ያገኘኋት ብዙ ገንዘብ ሰጥቼ ነው ” አለው፤ ጳውሎስም ፥ “እኔማ የተወለድሁ በዚያው ነው ” አለው።
[29] ከዚህም በኋላ ይመረምሩት ዘንድ የሚሹት ተዉት፤ የሻለቃውም ሮማዊ መሆኑን በዐወቀ ጊዜ “ ለምን አሰርሁት?” ብሎ ፈራ።
[30] በማግሥቱም የሻለቃው አይሁድ የሚከሱት ስለ ምን እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ወደደና ከእስራቱ ፈታው፤ ሊቃነ ካህናቱና ሸንጎውም ሁሉ እንዲመጡ አዘዘ፤ ጳውሎስንም አምጥቶ በፊታቸው አቆመው።