[1] ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ።
[2] አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊም አገኘ፤ የትውልድ ሀገሩም ጳንጦስ ነው፤ እርሱም ከጥቂት ወራት በፊት ከኢጣልያ ተሰዶ መጣ፤ ሚስቱ ጵርስቅላም አብራው ነበረች፤ ቀላውዴዎስ አይሁድ ከሮም እንዲሰደዱ አዝዞ ነበርና ወደ እነርሱ መጣ።
[3] ሥራቸው አንድ ስለ ነበረ ድንኳን ሰፊዎችም ስለ ነበሩ ከእነርሱ ጋር አብሮ ኖረ፤ በአንድነትም ይሠሩ ነበር።
[4] ጳውሎስም በየሰንበቱ በምኵuራብ ይከራከራቸው ነበር፤ አይሁድንና አረማውያንንም ያሳምናቸው ነበር።
[5] ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ቃሉን በማስተማር ይተጋ ነበር።
[6] እነርሱም በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ ፥ “እንግዲህ እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ነው፤ ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ ” አላቸው።
[7] ከዚያም አልፎ ስሙ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚፈራ ሰው ቤት ገባ፤ ቤቱም በምኵuራብ አጠገብ ነበር።
[8] የምኵuራብ አለቃ ቀርስጶስም ከነቤተ ሰቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ፤ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙዎች ሰምተው አምነው ተጠመቁ።
[9] ጌታችንም ጳውሎስን በሌሊት ራእይ እንዲህ አለው ፥ “አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር፥ ዝምም አትበል፤
[10] እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም ሊጐዳህ የሚነሣብህ የለም፤ በዚች ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና።”
[11] ጳውሎስም የእግዚአብሔርን ቃል እየአስተማራቸው ዓመት ከስድስት ወር በቆሮንቶስ ተቀመጠ።
[12] ጋልዮስም የአካይያ አገረ ገዢ በሆነ ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ሸንጎም አመጡት።
[13] እንዲህም አሉት ፥ “ይህ ሰው ኦሪትን በመቃወም እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ ሰዎችን ያባብላል።”
[14] ጳውሎስም ይመልስላቸው ዘንድ አፉን ሊከፍት ወድዶ ሳለ አገረ ገዢው ጋልዮስ መልሶ አይሁድን እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ አይሁድ ሆይ፥ የበደላችሁ በደል ቢኖር፥ ወይም ሌላ በደል ቢኖርበት አቤቱታችሁን በሰማሁና ባከራከርኋችሁ ነበር።
[15] ስለ ትምህርትና ስለ ስሞች፥ ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን ለራሳችሁ ዕወቁ፤ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ልሰማ አልፈቅድም።”
[16] ከሸንጎውም አባረራቸው።
[17] አረማውያንም ሁሉ የምኵuራቡን አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎ ፊት ደበደቡት፤ የእርሱም ነገር ጋልዮስን ምንም አላሳዘነውም።
[18] ጳውሎስም እንደ ገና በወንድሞቹ ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጠ፤ በሰላምም ሸኙትና ወደ ሶርያ በባሕር ተጓዘ፤ ጵርስቅላና አቂላም አብረውት ነበሩ፤ ስእለትም ነበረበትና በክንክራኦስ ራሱን ተላጨ።
[19] ወደ ኤፌሶንም ደረሱ፤ በዚያም ተዋቸውና እርሱ ብቻውን ወደ ምኵuራብ ገብቶ አይሁድን ተከራከራቸው።
[20] እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲሰነብት ማለዱት፤ ነገር ግን አልወደደም።
[21] ከዚህም በኋላ በሚሸኙት ጊዜ ፥ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንደገና እመለሳለሁ፤ አሁን ግን የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም ላደርግ እወዳለሁ ” አላቸው፤ ከኤፌሶንም በመርከብ ሄደ።
[22] ወደ ቂሳርያም ደረሰ፤ ከዚያም ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጿኪያ ሄደ።
[23] ጥቂት ቀንም ተቀመጠ፤ ከዚያም ወጥቶ በገላትያና በፍርግያ በኩል በተራ እየዞረ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም አጸናቸው።
[24] በእስክንድርያም የሚኖር፥ ንግግር የሚችልና መጽሐፍን የሚያውቅ አጵሎስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን መጣ።
[25] እርሱም የእግዚአብሔርን መንገድ የተማረ ነበር፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ሊያስተምርና ሊመሰክር ከልቡ የሚተጋ ነበር፤ ነገር ግን የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ተጠምቆ ነበር።
[26] እርሱም በምኵuራብ በግልጥ ይናገር ጀመር፤ ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ ወደ ማደሪያቸው ወስደው ፍጹም የእግዚአብሔርን መንገድ አስረዱት።
[27] ወደ አካይያም ሊሄድ በወደደ ጊዜ ወንድሞች አጽናኑት፤ እንዲቀበሉትም ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ ወደ እነርሱም በደረሰ ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ላመኑት ብዙ አስተማራቸው፤ ትልቅ ርዳታም ረዳቸው።
[28] ተሰብስበው ሳሉም በሕዝቡ ሁሉ ፊት አይሁድን በግልጥ እጅግ ይከራከራቸው ነበር፤ ስለ ኢየሱስም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት ማስረጃ ያመጣላቸው ነበር።