[1] ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያደርገውና ሊያስተምረው የጀመረውን ሥራ ሁሉ አስቀድሜ በመጽሐፍ ጽፌልሃለሁ።
[2] በመንፈስ ቅዱስ የመረጣቸው ሐዋርያትን አዝዞ እስከ ዐረገባት ቀን ድረስ ያለውን ጽፌልሃለሁ።
[3] ሕማማትን ከተቀበለ በኋላ ብዙ ተአምራት በማሳየት አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየነገራቸውና እያስተማራቸው ሕያው ሆኖ ራሱን ገለጠላቸው።
[4] ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ፥ “ከእኔ የሰማችሁትን የአብን ተስፋ ጠብቁ ” ብሎ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው።
[5] “ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን እስከ ቅርብ ቀን ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ” አላቸው።
[6] እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ ፥ “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት።
[7] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም።
[8] ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፥ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቼ ትሆኑኛላችሁ።”
[9] ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ከዐይናቸውም ተሰወረ።
[10] እነርሱም ወደ ሰማይ አተኵuረው ሲመለከቱ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች ነጫጭ ልብስ ለብሰው በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው።
[11] እነርሱም ፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየአያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፥ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል ” አሏቸው።
[12] ከዚህም በኋላ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ለኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
[13] ወደ ማደሪያቸውም በደረሱ ጊዜ ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ ማቴዎስ፥ በርተሎሜዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖን፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ።
[14] እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከጌታችን ከኢየሱስ እናት ከማርያም፥ ከወንድሞቹም ጋር በአንድነት ለጸሎት ይተጉ ነበር።
[15] ያንጊዜም ጴጥሮስ ተነሣና በወንድሞቹ መካከል ቆመ፤ መቶ ሃያ ያህል ሰዎችም በዚያ ሳሉ እንዲህ አላቸው።
[16] “እናንተ ሰዎች ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስሙ፤ ጌታችን ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባል።
[17] እርሱም ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበር፤ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበር።
[18] ከዚህም በኋላ ይህ ሰው በዐመፅ ዋጋዉ መሬት ገዛ፤ በምድር ላይም በግንባሩ ወደቀና ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ።
[19] በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ዜናዉ ተሰማ፤ ያም መሬት በቌንቌቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፤ ይኸውም የደም መሬት ማለት ነው።
[20] በመዝሙር መጽሐፍ ‘መኖሪያዉ ምድረ በዳ ትሁን፤ በውስጧም የሚኖር አይኑር፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ ’ ተብሎ ተጽፎአልና።
[21] እንግዲህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥
[22] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤዉ ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።”
[23] ኢዮስጦስ የሚሉትን በርናባስ የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን ሰዎች አቆሙ።
[24] እንዲህም ብለው ጸለዩ ፥ “አቤቱ፥ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ፥ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥኸውን አንዱን ግለጥ።
[25] ይሁዳ ወደ ሀገሩ ይሄድ ዘንድ የተዋትን ይህቺን የአገልግሎትና የሐዋርያነትን ቦታ የሚቀበላትን ግለጥ።”
[26] ዕጣም አጣጣሏቸው፤ ዕጣዉም በማትያስ ላይ ወጣ፤ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋራም ተቈጠረ።