[1] ክርክሩም ከተፈጸመ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን ጠራና አጽናናቸው፤ ተሰናበታቸውም፤ ወጥቶም ወደ መቄዶንያ ሄደ።
[2] በዚያ አውራጃም አልፎ ሄደ፤ በቃሉም ብዙ አስተማራቸው፤ ከዚያም በኋላ ወደ ግሪክ ሀገር ሄደ።
[3] በዚያም ሦስት ወር ተቀመጠ፤ ወደ ሶርያም በመርከብ ለመሄድ ዐስቦ ሳለ አይሁድ ስለ ተማከሩበት ወደ መቄዶንያ ሊመለስ ቈረጠ።
[4] ከእርሱም ጋር የቤርያ ሀገር ሰው የሚሆን ሱሲጳጥሮስ፥ የተሰሎንቄም ሰዎች አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ፥ የደርቤኑ ሰው ጋይዮስና ጢሞቴዎስም፥ የእስያ ሰዎች የሚሆኑ ቲኪቆስና ጥሮፊሞስም አብረውት ሄዱ።
[5] እነርሱም ቀድመውን ሄደው በጢሮአስ ቆዩን።
[6] እኛ ግን ከፋሲካ በኋላ ከፊልጵስዩስ ተነሥተን በባሕር ላይ ተጕuዘን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአስ ደረስን፤ በዚያም ሰባት ቀን ተቀመጥን።
[7] ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን እሑድ ማዕድ ለመባረክ ተሰብስበን ሳለን ጳውሎስ በማግሥቱ የሚሄድ ነውና ያስተምራቸው ጀመረ፤ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ድረስ ትምህርቱን አስረዘመ።
[8] ተሰብስበን በነበርንበት ሰገነትም ብዙ መብራት ነበር።
[9] ስሙ አውጤክስ የሚባል አንድ ጐልማሳ ልጅም በመስኮት በኩል ተቀምጦ ሳለ ከባድ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ትምህርቱን ባስረዘመ ጊዜ ያ ጐልማሳ ከእንቅልፉ ብዛት የተነሣ ከተኛበት ከሦስተኛው ፎቅ ወደ ታች ወደቀ፤ ሬሳውንም አነሡት።
[10] ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፤ አቅፎም ያዘው፤ እነርሱንም ፥ “ነፍሱ አለችና አትደንግጡ ” አላቸው።
[11] ከዚህም በኋላ ወደ ሰገነት ወጣ፤ ማዕዱንም ባርኮ በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ብዙ ትምህርት አስተማራቸው፤ ከዚያ በኋላም ተነሥቶ ሄደ።
[12] ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት፤ እጅግም ደስ አላቸው።
[13] እኛ ግን በመርከብ ሆነን ወደ አሶስ ሄድን፤ ከዚያ ጳውሎስን ልንቀበለው እንሻ ነበርና፤ እንደዚሁ በእግር እንደሚመጣ ነግሮን ነበርና ተቀበልነው።
[14] አሶስም ደረስን፤ በመርከብም ይዘነው ወደ ሚጢሊኒ ሄድን።
[15] በማግሥቱም ከዚያ ወጥተን በኪዮስ ፊት ለፊት ደረስን፤ በማግሥቱም ወደ ሳሞስ አለፍን፤ በትሮጊሊዮም ተቀመጥን፤ ከዚህ ቀን በኋላም ወደ መሊጡ ደረስን።
[16] ጳውሎስም በእስያ እንዳይዘገይ በኤፌሶን በኩል ሊሄድ ቈርጦ ነበር፤ የሚቻለውም ቢሆን ለበዓለ ኀምሳ ኢየሩሳሌም ለመድረስ ቸኵuሎ ነበርና።
[17] ከመሊጡም የቤተ ክርስቲያንን ቀሳውስት ይጠሩአቸው ዘንድ ወደ ኤፌሶን ላከ።
[18] ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው ፥ “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ዘንድ እንደ ተቀመጥሁ እናንተ ታውቃላችሁ።
[19] እግዚአብሔርን እያገለገልሁ በፍጹም መከራና በልቅሶ ከአይሁድም ሴራ የተነሣ በደረሰብኝ ፈተና እየተጋደልሁ፥
[20] በጉባኤም ሆነ በቤት ስነግራችሁና ሳስተምራችሁ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳን አላስቀረሁባችሁም።
[21] ወደ እግዚአብሔር መመለስንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለአረማውያን እየመሰከርሁ፤
[22] አሁንም እነሆ በመንፈስ ታሥሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ ነገር ግን በዚያ የሚያገኘኝን አላውቅም።
[23] ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ፥ በየከተማው መከራና እስራት ይጠብቅሃል ብሎ ይመሰክርልኛል።
[24] ነገር ግን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ወንጌል እንዳስተምር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልሁትን ሩጫዬን እንድጨርስና መልእክቴንም እንድፈጽም ነው እንጂ ለሰውነቴ ምንም አላስብላትም።
[25] አሁንም እነሆ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ እናንተ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንደማታዩኝ እኔ ዐውቄአለሁ።
[26] እኔ ከሁላችሁም ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ እነሆ ዛሬ በዚች ሌሊት እመሰክርላችኋለሁ።
[27] ከእግዚአብሔር ምክር ሁሉ የሰወርኋችሁና ያልነገርኋችሁ የለም።
[28] አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
[29] ከእኔ በኋላ ለመንጋዪቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኵuላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ።
[30] ደቀ መዛሙርትንም ወደ እነርሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ከእናንተ መካከል ይነሣሉ።
[31] ስለዚህም ትጉ፤ እኔ ሁላችሁንም ሳስተምር ሦስት ዓመት ሙሉ ሌትም ቀንም እንባዬ እንዳልተገታ ዐስቡ።
[32] አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያንጻችሁ፥ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።
[33] ወርቅም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን፥ ልብስም ቢሆን ከእናንተ ከአንዱ ስንኳ አልተመኘሁም።
[34] እነዚህም እጆቼ ለምሻው ነገርና ከእኔም ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ።
[35] በድካማችንና በሥራችን ነዳያንን እንቀበላቸው ዘንድ እንደሚገባን ይህን አስተምሬአችኋለሁ፤ ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው ’ ያለውንም የጌታችንን የኢየሱስን ቃል ዐስቡ።”
[36] ይህንም ከአለ በኋላ ተንበርክኮ አብረውት ካሉት ሁሉ ጋር ጸለየ።
[37] ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ሳሙት።
[38] ይልቁንም “ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩትም ” ስለ አላቸው እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት።