Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:25

[1] ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩ ወንድሞችም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።

[2] ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከአይሁድ ወገን የሆኑት ወንድሞች ተቃወሙት።

[3] “ወደ አልተገረዙት ሰዎች ቤት ገብተህ አብረሃቸው በልተሃል ” አሉት።

[4] ጴጥሮስም ከመጀመሪያ ጀምሮ ይነግራቸው ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው።

[5] “በኢዮጴ ከተማ ሳለሁ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝና ራእይ አየሁ፤ ታላቅ መጋረጃ የመሰለ ዕቃ በአራቱ ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ወደ እኔም መጣ።

[6] በውስጡም አራት እግር ያላቸው እንስሳንና አራዊትን፥ ተንቀሳቃሾችንም፥ የሰማይ ወፎችንም አየሁ።

[7] ‘ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ ’ የሚለኝንም ቃል ሰማሁ።

[8] ‘አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ንጹሕ ያልሆነ ርኩስ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም ’ አልሁ።

[9] ደግሞም ፥ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክሰው ’ የሚል ቃል ከሰማይ መለሰልኝ።

[10] እንዲህም መላልሶ ሦስት ጊዜ ነገረኝ፤ ዳግመኛም ሁሉ ተጠቅልሎ ወደ ሰማይ ተመለሰ።

[11] በዚያችም ሰዓት ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች መጡ፤ እኔ ባለሁበት ግቢ በርም ቆሙ።

[12] መንፈስ ቅዱስም ፥ ‘ሳትጠራጠር አብረሃቸው ሂድ ’ አለኝ፤ እነዚህ ስድስቱ ወንድሞቻችንም ተከትለውኝ መጡና ወደዚያ ሰው ቤት ገባን።

[13] እርሱም በቤቱ ቆሞ ሳለ የእግዚአብሔርን መልአክ እንዳየ ‘ወደ ኢዮጴ ከተማ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ።

[14] አንተና ቤተ ሰቦችህ ሁሉ የምትድኑበትን ነገር እርሱ ይነግርሃል ’ እንደ አለው ነገረን።

[15] ላስተምራቸው በጀመርሁ ጊዜም ቀድሞ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱም ላይ ወረደ።

[16] ‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን፤ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ’ ያለውን የጌታችንን ቃል ዐሰብሁ።

[17] እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለአመንነው ለእኛ እንደ ሰጠን፥ ያን ጸጋውን እንደ እኛ አስተካክሎ ከሰጣቸው እግዚአብሔርን ልከለክል የምችል እኔ ማነኝ?”

[18] ይህንም በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ ፥ “እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሓን ሰጣቸው እንጃ ” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

[19] በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት የተበተኑት ግን፤ ወደ ፊንቄ ወደ ቆጵሮስና ወደ አንጿኪያ ደረሱ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድስ እንኳ አይናገሩም ነበር።

[20] ከመካከላቸውም ወደ አንጿኪያ ሄደው ለአረማውያን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገር ያስተማሩ የቆጵሮስና የቄሬና ሰዎች ነበሩ።

[21] የእግዚአብሔርም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ወደ ጌታም ተመልሰው ያመኑ ሰዎች ቐጥራቸው በዛ።

[22] ስለ እነርሱ የተነገረውም ይህ ነገር በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተሰማ፤ በርናባስንም ወደ አንጿኪያ ላኩት።

[23] በደረሰ ጊዜም የእግዚአብሔርን ጸጋ አየና ደስ አለው፤ በፍጹም ልባቸውም በእግዚአብሔር ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው።

[24] ደግ ሰው፥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት፥ ሃይማኖተኛም ነበርና፤ በጌታችንም አምነው ብዙዎች አሕዛብ ተጨመሩ።

[25] ከዚህም በኋላ በርናባስ ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤ በአገኘውም ጊዜ ወደ አንጿኪያ ወሰደው።

[26] በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት አብረው ተቀመጡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጿኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ።

[27] ያንጊዜም ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጿኪያ ወረዱ።

[28] ከመካከላቸውም አጋቦስ የተባለ አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ጽኑ ረኃብ እንደሚመጣ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ተናገረ፤ ይህም በቄሣር ቀላውዴዎስ ዘመን ሆነ።

[29] ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርት እያንዳንዳቸው የሚችሉትን ያህል አወጣጥተው በይሁዳ ሀገር ለሚኖሩት ወንድሞቻቸው ርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ።

[30] እንደዚህም አድርገው በበርናባስና በሳውል እጅ ወደ ቀሳውስት ላኩት።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters