Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:35

[1] አግሪጳም ጳውሎስን ፥ “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ፈቅደንልሃል ” አለው፤ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጁን አነሣና ይነግራቸው ጀመር፤ እንዲህም አለ ፥

[2] “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አይሁድ እኔን ስለ ከሰሱበት ነገር ሁሉ ዛሬ በአንተ ዳኝነት እከራከር ዘንድ ስለ ተገባኝ ራሴን እንደ ተመሰገነ አድርጌ እቈጥረዋለሁ።

[3] የአይሁድን ጠባያቸውንና ክርክራቸውን አጥብቀህ ታውቃለህና ታግሠህ ታደምጠኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

[4] “ከልጅነቴ ጀምሮ በወገኖቼ መካከል በኢየሩሳሌም የኖርሁትን ኑሮ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ።

[5] ሊመሰክሩም ከወደዱ እኔ ፈሪሳዊ ሆኜ በአባቶቻችን ሕግ እንደምኖር ከጥንት ጀምሮ እነርሱ ያውቁልኛል።

[6] አሁንም ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን የተሰጠውን ተስፋ በመታመን ከፍርድ በታች ቆሜአለሁ።

[7] ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን በመዓልትም በሌሊትም እርሱን እያገለገሉ ወደ እርስዋ ይደርሱ ዘንድ ተስፋ ያደርጋሉ፤ አይሁድም የሚከስሱኝ ስለዚህ ተስፋ ነው።

[8] እንዴትስ እግዚአብሔር ሙታንን እንደሚያስነሣቸው በእናንተ ዘንድ የማይታመን ሆኖ ይቈጠራል?

[9] “እኔም ብዙ ጊዜ በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም ላይ ክፉ ነገር ላደርግ ቈርጬ ነበር።

[10] ይህንም በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከሊቃነ ካህናትም ሥልጣን ተቀብዬ ከቅዱሳን ብዙዎችን ወደ ወኅኒ ቤት አስገባኋቸው፤ ሲገድሏቸውም አብሬ እመክር ነበርሁ።

[11] በየምኵuራቡ ሁሉ የማስገደጃ ማዘዣ አምጥቼ፥ በግድ የኢየሱስን ስም እንዲሰድቡ ዘወትር መከራ አጸናባቸው ነበር፤ ይልቁንም ወደ ሌሎች ከተማዎች እያሳደድሁ ከፋሁባቸው።

[12] “ይህንም ለመፈጸም ከሊቃነ ካህናት ሥልጣን ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ከተማ ሄድሁ።

[13] ንጉሥ ሆይ፥ እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ ስሄድ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ።

[14] ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ በዕብራይስጥ ቌንቌ ፥ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? በሾለ ብረት ላይ መርገጥ ለአንተ ይብስሃል ’ የሚለኝን ቃል ሰማሁ።

[15] እኔም ፥ ‘አቤቱ አንተ ማነህ?’ አልሁ፤ ጌታም አለኝ ፥ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።

[16] ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ እኔን ባየህበትና ወደፊትም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር አድርጌ ልሾምህ ስለዚህ ተገልጬልሃለሁና።

[17] እኔም ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።

[18] ይኸውም ዐይናቸውን ትከፍትላቸው ዘንድ፥ ከጨለማም ወደ ብርሃን፥ ሰይጣንን ከማምለክም ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸው ዘንድ፥ ኀጢአታቸውም ይሰረይላቸው ዘንድ፥ በስሜም በማመን ከቅዱሳን ጋር አንድነትን ያገኙ ዘንድ ነው።’

[19] “አሁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከሰማይ የተገለጠልኝን ራእይ አልካድሁም።

[20] አስቀድሜ በኢየሩሳሌምና በደማስቆ ላሉት፥ ለይሁዳ አውራጃዎችም ሁሉ ነገርኋቸው፤ ለአሕዛብም ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ፥ ለንስሓቸውም የሚገባ ሥራን ይሠሩ ዘንድ አስተማርኋቸው።

[21] ሰለዚህም ብቻ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ወደዱ።

[22] እግዚአብሔርም አዳነኝና ለታላቁም፥ ለታናሹም እየመሰከርሁ እስከ ዛሬ ደረስሁ፤ ይደረግ ዘንድ ካለው፥ ነቢያት ከተናገሩት፥ ሙሴም ከተናገረው ሌላ ያስተማርሁት የለም።

[23] ክርስቶስ እንደሚሞት፥ ከሙታን ተለይቶም አስቀድሞ እንደሚነሣ፥ ለሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ፥ ለመላውም ዓለም እንደሚያበራ።”

[24] ይህንም ስለ ራሱ ሲናገር ሀገረ ገዢው ፊስጦስ መለሰ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ ፥ “ጳውሎስ ሆይ፥ ልታብድ ነውን? ብዙ ትምህርት እኮ ልብን ይነሣል ” አለው።

[25] ጳውሎስም እንዲህ አለው ፥ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ እውነትና የተጣራ ነገርን እናገራለሁ እንጂ ዕብደትስ የለብኝም።

[26] በፊቱ ገልጬ የምናገርለት እርሱ ራሱ ንጉሥ አግሪጳ ያውቅልኛል፤ ከዚህም የሚሳተው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ ወደ ጎን የተሰወረ አይደለምና።

[27] ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እነሆ፥ በነቢያት ቃል ታምናለህን? እንደምታምንም አውቃለሁ።”

[28] አግሪጳም ጳውሎስን ፥ “አሁንስ ወደ ክርስቲያንነት ልታገባኝ ጥቂት ብቻ ቀርቶሃል ” አለው።

[29] ጳውሎስም ፥ “በጥቂትም ቢሆን፥ በብዙም ቢሆን አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ።”

[30] ከዚህም በኋላ ንጉሡ፥ ሀገረ ገዥውም፥ በርኒቄም፥ ሹሞቻቸውም ተነሡ።

[31] ለብቻቸውም ገለል ብለው እርስ በርሳቸው እንዲህ ብለው ተነጋገሩ ፥ “ይህ ሰው እንዲሞት ወይም እንዲታሰር የሚያበቃ የሠራው በደል የለም።”

[32] አግሪጳም ፊስጦስን ፥ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ኖሮ ይህ ሰው ይፈታ ዘንድ በተገባ ነበር ” አለው።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters