Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:45

[1] ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ወደ ቄሣር ወደ ኢጣልያ በመርከብ እንሄድ ዘንድ ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስ ከሌሎች እስረኟች ጋር አብሮ የአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚባል የመቶ አለቃ ተሰጠ።

[2] በተነሣንም ጊዜ ወደ እስያ በምትሄድ በአድራማጢስ መርከብ ተሳፈርን፤ የተሰሎንቄ ሀገር ሰው የሚሆን መቄዶንያዊው አርስጥሮኮስም አብሮን ሄደ።

[3] በማግሥቱም ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ አዘነለት፤ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና በእነርሱ ዘንድ እንዲያርፍም ፈቀደለት።

[4] ከዚያም ወጥተን ነፋስ ፊት ለፊት ነበርና በቆጵሮስ በኩል ዐለፍን።

[5] ወደ ኪልቅያና ወደ ጵንፍልያ ባሕርም ገብተን የሉቅያ ክፍል ወደምትሆነው ወደ ሙራ ሄድን።

[6] በዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣልያ የምትሄድ የእስክንድርያን መርከብ አገኘ፤ ወደ እርስዋም አስገባን።

[7] ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄድን፤ በጭንቅም ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ወደዚያም በቀጥታ ለመድረስ ነፋስ ቢከለክለን በቀርጤስ በኩል በሰልሙና ፊት ለፊት ዐለፍን።

[8] ባጠገብዋም በጭንቅ ስናልፍ ላሲያ ለምትባለው ከተማ አቅራቢያ ወደ ሆነችው መልካም ወደብ ወደምትባለው ቦታ ደረስን።

[9] በዚያም ብዙ ቀን ቈየን፤ የአይሁድም የጿም ወራት አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መከራቸው።

[10] “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ስሙኝ፤ ጕuዞአችን በብዙ ጭንቀትና በከባድ ጥፋት ላይ ሆኖ አያለሁ፤ ይህንም የምለው ጥፋቱ በራሳችንም ሕይወት እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ ስላልሆነ ነው።”

[11] የመቶ አለቃው ግን ለመርከቡ ባለቤትና ለመሪው ይታዘዝ ነበር፤ የጳውሎስን ቃል ግን አይቀበልም ነበር።

[12] ያም ወደብ ክረምቱን ሊከርሙበት የማይመች ነበር፤ ስለዚህም ብዙዎች ከዚያ ይወጡ ዘንድ ይቻላቸው እንደ ሆነ በቀኝ በኩል ወደ አለው ፊንቄ ወደሚባለው ወደ ሁለተኛው የቀርጤስ ወደብ ይደርሱ ዘንድ ወደዱ።

[13] ልከኛ የአዜብ ነፋስም ነፈሰ፤ እነርሱም እንደ ወደዱ የሚደርሱ መስሎአቸው ነበር፤ መልሕቁንም አነሡ፤ በቀርጤስም አጠገብ ሄዱ።

[14] ከጥቂት ጊዜ በኋላም አውራቂስ የሚሉት ጽኑዕ ዓውሎ ነፋስ መጣ።

[15] መርከባችንም ተመትታ ተነጠቀች፤ ቀዛፊዎችም በነፋሱ ፊት ለፊት መቆም አልተቻላቸውምና ተዉአት፤ ብቻዋንም ሄደች።

[16] ከዚህም በኋላ ቄዳ ወደምትባል ደሴት እስክንገባ ድረስ ነፋሱ ነፈሰ፤ በጭንቅም ታንኳችንን ለመግታት ቻልን።

[17] ከዚህ በኋላ ተጋግዘን በገመድ አጠናከርናት፤ ከዚህም ቀጥሎ ቀዛፊዎች ወደ ጥልቁ ባሕር እንዳይወድቁ በፈሩ ጊዜ ሸራውን አወረዱ፤እንዲሁም እንድንሄድ አደረግን።

[18] በማግሥቱም ማዕበል ጸናብን፤ ከጭነቱም ወደ ባሕር ጣልን።

[19] በሦስተኛውም ቀን በመርከብ ያለውን ሁሉ በእጃችን እያነሣን በባሕር ላይ ጣልን።

[20] ብዙ ቀንም ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም ሳናይ ማዕበሉ ጸናብን፤ ለመዳንም ተስፋ ቈርጠን ነበር።

[21] ከእኛም መብል የበላ አልነበረም። ጳውሎስም ተነሥቶ በመካከል ቆመና እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ቀድሞ ቃሌን ሰምታችሁኝ ቢሆን ከቀርጤስም ባትወጡ ኖሮ ከዚህ ጕuዳትና መከራ በዳናችሁ ነበር።

[22] አሁንም እላችኋለሁ፤ መርከባችን እንጂ ከመካከላችን አንድ ሰው ስንኳ አይጠፋምና አትፍሩ።

[23] እኔ ለእርሱ የምሆንና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና።

[24] እርሱም እንዲህ አለኝ ፥ ‘ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ ከአንተም ጋር የሚሄዱትን ሁሉ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለአንተ ሰጥቶሃል።’

[25] አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ እንደ ነገረኝ እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና።

[26] ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንደርሳለን።”

[27] በዐሥራ አራተኛውም ቀን በመንፈቀ ሌሊት በአድርያ ባሕር ስንጓዝ ቀዛፊዎች ወደ የብሱ የደረሱ መሰላቸው።

[28] መለኪያ ገመድ ጣሉ፤ በሰው ቁመትም ሃያ አገኙ፤ ከዚያም ጥቂት ፈቀቅ ብለው ዳግመኛ ጣሉ፤ በሰው ቁመትም ዐሥራ አምስት አገኙ።

[29] ድንጋያማ በሆነ ቦታም እንዳይወድቁ ፈሩ፤ ስለዚህም ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ በባሕሩ ላይ ጣሉ፤ ፈጥኖ እንዲነጋም ጸለዩ።

[30] ከዚህ በኋላም ቀዛፊዎቹ ከመርከብ ሊኮበልሉ በወደዱ ጊዜ ወደ ኋላ ሊመለሱ ከምድር ላይ ሆነው መርከባቸውን የሚያጠናክሩ መስለው ጀልባቸውን ወደ ባሕር አወረዱ።

[31] ጳውሎስም ይህን ባየ ጊዜ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ ፥ “እነዚህ ቀዛፊዎች በመርከብ ውስጥ ከሌሉ መዳን አትችሉም ” አላቸው።

[32] ወታደሮችም ወዲያውኑ ተነሥተው የታንኳዪቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት።

[33] ሊነጋም በጀመረ ጊዜ ጳውሎስ እህል እንዲበሉ ሁሉንም ማለዳቸው፤ እንዲህም አላቸው ፥ “እህል ከተዋችሁ ዛሬ ዐሥራ አራት ቀን ነው።

[34] አሁንም እሺ በሉኝና ምግብ ብሉ፤ ራሳችሁንም አድኑ፥ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕuር እንኳ አትጠፋምና።”

[35] ይህንም ተናግሮ ኅብስቱን አንሥቶ በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ።

[36] ሁሉም ተጽናኑ፤ እህልም ቀመሱ።

[37] በመርከቡ ውስጥ የነበሩትም ቐጥራቸው ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበር።

[38] በልተውም በጠገቡ ጊዜ በመርከቡ ውስጥ የነበረውን ስንዴ ወደ ባሕር ጣሉት፤ መርከቡንም አቃለሉ።

[39] በነጋ ጊዜም ቀዛፊዎች ቦታውን አልለዩም፤ የሚሄዱበትንም አላወቁም፤ ነገር ግን ለባሕሩ አቅራቢያ የሆነውን የደሴት ተራሮች አዩ፤ መርከባቸውንም ወደ እዚያ ሊያስጠጉ ፈለጉ።

[40] መልሕቁንም ፈትተው በባሕር ላይ ጣሉት፤ የሚያቆሙበትንም አመቻችተው እንደ ነፋሱ አነፋፈስ መጠን ትንሹን ሸራ ሰቀሉ፤ ወደ ባሕሩ ዳርቻም ሄድን።

[41] መርከቢቱም በሁለት ታላላቅ ድንጋዮች መካከል ተቀረቀረች፤ ባሕሩም ጥልቅ ነበረ። ከወደፊቷም ተያዘች፤ አልተንቀሳቀሰችምም፤ ከሞገዱም የተነሣ በስተኋላ በኩል ጎንዋን ተሰብራ ተጐረደች፤ ቀዛፊዎችም ወደፊት ሊገፉአት አልቻሉም።

[42] ወታደሮቹም ዋኝተው እንዳያመልጡ እስረኟችን ለመግደል ተማከሩ።

[43] የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ሊያድነው ወድዶአልና ምክራቸውን እንቢ አለ፤ ዋና የሚያውቁትንም ዋኝተው ወደ ምድር እንዲወጡ አዘዛቸው።

[44] የቀሩትም በመርከቡ ስብርባሪ ዕንጨትና በሳንቃው ላይ ተሻገሩ፤ ሌሎችም በመርከቡ ገመድ ላይ እየተንጠላጠሉ ተሻገሩ፤ ሁሉም እንዲህ ባለ ሁኔታ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters