[1] ከዚህም በኋላ በደኅና በደረስን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባል ዐወቅን።
[2] በዚያ የሚኖሩት አረማውያንም አዘኑልን፤ መልካም ነገርንም አደረጉልን፤ ከቐሩም ጽናትና ከዝናሙ ብዛት የተነሣ እሳት አንድደው እንድንሞቅ ሁላችንንም ሰበሰቡን።
[3] ጳውሎስም ብዙ ጭራሮ ሰብስቦ በእሳቱ ላይ ጨመረው፤ እፉኝትም ከእሳቱ ወላፈን የተነሣ ወጥታ ጳውሎስን እጁን ነደፈችው።
[4] አረማውያንም እፉኝቱ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ፥ “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል፤ ከባሕር እንኳ በደኅና ቢወጣም በሕይወት ይኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ አልተወውም ” አሉ።
[5] ጳውሎስ ግን እጁን አራግፎ እፉኝቱን በእሳት ውስጥ ጣላት፤ ጕuዳትም አላገኘውም።
[6] እነርሱ ግን ወዲያውኑ የሚያብጥ ወይም ሞቶ የሚወድቅ መስሎአቸው ነበር። እያዩትም ብዙ ሰዓት ቆሙ፤ አንዳችም እንደ አልጐዳው በአዩ ጊዜም ፥ “ይህስ አምላክ ነው ” ብለው ቃላቸውን ለወጡ።
[7] በዚያ ቦታም አጠገብ ስሙን ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴቲቱ አለቃ መሬት ነበር፤ እርሱም ሦስት ቀን ሙሉ በደስታ በቤቱ ተቀብሎ አስተናገደን።
[8] የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ይኖር ነበር፤ ጳውሎስም እርሱ ወዳለበት ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው።
[9] ያደረገውንም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ በዚያች ደሴት ያሉትን ድውያን ሁሉ አመጡለት፤ ፈወሳቸውም።
[10] እጅግ ታላቅ ክብርም አከበሩን፤ ከእነርሱም ዘንድ ለመሄድ በተነሣን ጊዜ የሚያስፈልገንን ስንቅ ሰጡን።
[11] ከሦስት ወር በኋላም በዚያች ደሴት ወደ ከረመችው ወደ እስክንድርያ መርከብ ወጣን፤ በዚያች መርከብ ላይም የዲዮስቆሮስ ምልክት ነበረባት፤ ይኸውም “የመርከበኟች አምላክ ” የሚሉት ነው።
[12] ከዚያም ሄደን ወደ ሰራኩስ ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን።
[13] ከዚያም ሄደን ሬቅዩን ወደምትባል ሀገር ደረስን፤ በማግሥቱም ወጣን፤ ከአንድ ቀንም በኋላ ከጐንዋ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ደረስን።
[14] በዚያም ወንድሞችን አግኝተን ተቀበሉን፤ በእነርሱ ዘንድም ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ሄደን ወደ ሮሜ ደረስን።
[15] በዚያም ያሉት ወንድሞች ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ፤ አፍዩስ ፋሩስ እስከሚባለው ገበያና እስከ ሦስተኛው ማረፊያ ድረስ ወጥተው ተቀበሉን፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና።
[16] ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ የመቶ አለቃው እስረኟችን ለሠራዊቱ አለቃ አስረከበ፤ ጳውሎስ ግን ከሚጠብቀው አንድ ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ፈቀደለት።
[17] ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች ሰበሰባቸው፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው ፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ በሕዝቡም ላይ ቢሆን፥ በአባቶቻችንም ሕግ ላይ ቢሆን ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ ለሮም ሰዎች አሳልፈው ሰጡኝ።
[18] እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስለአላገኙብኝ ሊፈቱኝ ወደዱ።
[19] አይሁድ ግን ሊቃወሙኝ በተነሡ ጊዜ ወደ ቄሣር ይግባኝ ለማለት ግድ ሆነብኝ፤ ነገር ግን ወገኖቼን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።
[20] ስለዚህም ላያችሁ፥ ልነግራችሁና ላስረዳችሁ ወደ እኔ እንድትመጡ ማለድኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ በዚህ ሰንሰለት ታስሬአለሁና።”
[21] የአይሁድ ታላላቅ ሰዎችም እንዲህ አሉት ፥ “ለእኛስ ከይሁዳ ሀገር ስለ አንተ መልእክት አልደረሰንም፤ ከኢየሩሳሌም ከመጡት ወንድሞችም ቢሆን አንድ ስንኳ ከዚህ አስቀድሞ ስለ አንተ ክፉ ነገር ያወራን፥ የነገረንም የለም።
[22] ነገር ግን በዚህ ነገር በየስፍራው ሁሉ እንዲጣሉ በእኛ ዘንድ ታውቌልና የአንተን ዐሳብ ደግሞ ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንወድዳለን።”
[23] ከዚህም በኋላ ወደ እርሱ የሚመጡበትን ቀን ቀጠሩትና ብዙዎች ወዳረፈበት ወደ እርሱ መጡ፤ ከጥዋትም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ኦሪትና ከነቢያት እየጠቀሰ ነገራቸው።
[24] ከእነርሱም እኩሌቶቹ የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አልተቀበሉትም።
[25] እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ከእርሱ ተመለሱ፤ እንዲህም አላቸው ፥ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት ለአባቶቻችን በእውነት እንዲህ ብሎ መልካም ነገር ተናግሮአል።
[26] ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና እንዲህ በላቸው ፥ መስማትን ትሰማላችሁ፤ ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ግን አትመለከቱም።
[27] በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ወደ እኔም እንዳይመለሱና ይቅር እንዳልላቸው የዚህ ሕዝብ ልባቸው ደንድኖአልና፥ ጆሮአቸውም ደንቁሮአልና፥ ዐይናቸውንም ጨፍነዋልና’።
[28] እንግዲህ ከእግዚአብሔር የተገኘች ይህቺ ድኅነት ለአሕዛብ እንደምትሆን ዕወቁ፤ እነርሱም ይሰሙታል።”
[29] ይህንም በተናገራቸው ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ወጥተው ሄዱ።
[30] ጳውሎስም በገንዘቡ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጣውንም ሁሉ ይቀበል ነበር።
[31] ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሰብክ ነበር፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።
[32] ጳውሎስም በመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኔሮን ቄሣር ገብቶ ነበርና ረትቶ በሰላም ሄደ፤ ከዚህም በኋላ ሁለት ዓመት ኖሮ ከሮም ወጣ።
[33] ከዚህም በኋላ ወደ ሮም ተመልሶ የኔሮን ቄሣር ዘመዶችን አጠመቀ፤ በኔሮን ትእዛዝም በሰይፍ ተመትቶ መከራውንም ታግሦ ሰማዕት ሆነ። ወንጌላዊው ሉቃስ የጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተፈጸመ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።