Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 7:28

[1] ኀምሳው ቀንም በተፈጸመ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድነት በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር።

[2] ድንገትም እንደ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ የነበሩበትንም ቤት ሞላው።

[3] እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም ታዩአቸው፤ በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው።

[4] ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደ አደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገሩ ሁሉ ቌንቌ ይናገሩ ጀመሩ።

[5] ከሰማይ በታች ካሉ አሕዛብ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደጋግ የአይሁድ ሰዎች ነበሩ።

[6] ይህንም ቃል ሲናገሩ ሰምተው ሁሉም ደንግጠው ተሰበሰቡ፤ ሁሉም በየሀገራቸው ቌንቌ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋልና የሚሉትን አጡ።

[7] ተገረሙ፤ አደነቁም፥ እንዲህም አሉ ፥ “እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

[8] እንግዲህ በየሀገራችን ቌንቌ ሲናገሩ እንዴት እንሰማቸዋለን?

[9] እኛ በተወለድንበት በጳርቴ፥ በሜድ፥ በኢላሜጤ፥ በሁለቱ ወንዞች መካከል፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስና በእስያ፥

[10] በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብፅ፥ በሊብያ አውራጃ፥ በቀርኔን የምንኖር፥ ከሮሜም የመጣን አይሁድ፥ መጻተኟችም፥

[11] ከቀርጤስና ከዐረብም የመጣን፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ጌትነት በየሀገራችን ቌንቌ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።”

[12] ሁሉም ተገረሙ፤ የሚሉትንም አጡ፥ እርስ በርሳቸውም ፥ “እንጃ! ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።

[13] እኩሌቶቹ ግን “እነዚህስ ጉሽ ጠጅ ጠግበው ሰክረዋል ” ብለው ሳቁባቸው።

[14] ጴጥሮስም ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ ፥ “እናንተ የአይሁድ ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ ይህን ዕወቁ፤ ቃሌንም ስሙ።

[15] ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና።

[16] ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው።

[17] በኋለኛዪቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል እግዚአብሔር ፥ ሥጋን በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁ ራእይን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ።

[18] በወንዶችና በሴቶች ባሮቼ ላይም ያንጊዜ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ።

[19] በላይ በሰማይ ተአምራትን፥ በታች በምድርም ምልክቶችን፥ ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ።

[20] የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።

[21] የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።

[22] “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ነገር ስሙ፤ እንደምታውቁት በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእጁ ባደረገው በከሃሊነቱ በተአምራቱና በድንቅ ሥራዎቹ እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ሰው የናዝሬቱን ኢየሱስን ስሙ።

[23] እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት።

[24] እግዚአብሔር ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና።

[25] ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ አለ ፥ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።

[26] ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ።

[27] ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና።

[28] የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ።

[29] “እናንተ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት ነገር እንደ ሞተ እንደ ተቀበረም፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደ አለ ገልጬ እንድነግራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን?

[30] ነቢይ ስለ ነበረ፥ ከአብራኩም የተገኘውን በዙፋኑ እንዲያነግሥለት እግዚአብሔር መሐላን እንደ ማለለት ስለ ዐወቀ፥

[31] ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፥ ሥጋዉም በመቃብር እንደማይቀር፥ ጥፋትንም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ።

[32] እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮቹ ነን።

[33] አሁን ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ገንዘብ አድርጎ ይህን ዛሬ የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

[34] ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፥ ነገር ግን እርሱ አለ ፥ ጌታ ጌታዬን አለው ፥ በቀኜ ተቀመጥ።

[35] ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስክጥላቸው ድረስ።

[36] እንግዲህ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም መሢሕም እንዳደረገው በርግጥ ይወቁ።”

[37] ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተከፈተ፤ ጴጥሮስንና ወንድሞቹ ሐዋርያትንም ፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሏቸው።

[38] ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው ፥ “ንስሓ ግቡ፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፤ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ።

[39] ተስፋዉ ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ እግዚአብሔር አምላካችንም ለሚጠራቸው ርቀው ለነበሩ ሁሉ ነውና።”

[40] ሌላም ብዙ ነገር ነገራቸው፤ “ከዚህ ከክፉ ዓለምም ነፍሳችሁን አድኑ ” ብሎ መከራቸው።

[41] ቃሉንም ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚችም ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ተጨመሩ።

[42] በሐዋርያት ትምህርትና በአንድነት ማዕድን በመባረክ፥ በጸሎትም ጸንተው ይኖሩ ነበር።

[43] ሰው ሁሉ ፈራቸው፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ተአምራትና ድንቅ ሥራ ይደረግ ነበር።

[44] ያመኑትም ሁሉ በአንድነት ይኖሩ ነበር፤ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበር።

[45] መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ እንደሚያሻው ይሰጡ ነበር።

[46] ሁልጊዜም አንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደስ ያገለግሉ ነበር፤ በቤትም ኅብስትን ይቈርሱ ነበር፤ በደስታና በልብ ቅንንነትም ምግባቸውን ይመገቡ ነበር።

[47] እግዚአብሔርንም ያመሰግኑ ነበር፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ መወደድ ነበራቸው፤ እግዚአብሔርም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters