[1] በዚያ ወራትም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ከሐዋርያትም በቀር ሁሉም በይሁዳና በሰማርያ ባሉ አውራጃዎች ሁሉ ተበተኑ።
[2] እስጢፋኖስንም ደጋግ ሰዎች አንሥተው ቀበሩት፤ ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት።
[3] ሳውል ግን ገና አብያተ ክርስቲያናትን ይቃወም ነበር፤ የሰውንም ቤት ሁሉ ይበረብር ነበር፤ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።
[4] የተበተኑት ግን እየተዘዋወሩ የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፥ አስተማሩም።
[5] ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወረደ፤ ስለ ክርስቶስም ሰበከላቸው።
[6] ሕዝቡም የነገራቸውን በሰሙና ያደርገው የነበረውን ተአምራት በአዩ ጊዜ በአንድ ልብ የፊልጶስን ነገር ተቀበሉ።
[7] ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸውም ብዙዎች ነበሩና፥ በታላቅ ቃል እየጮኹ ይወጡ ነበር፤ ብዙዎች ልምሾዎችና አንካሶችም ይፈወሱ ነበር።
[8] በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ።
[9] በዚያችም ከተማ ሲሞን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ የሰማርያ ሰዎችንም ያስት ነበር፤ ሰውየዉ ሥራየኛ ነበር፤ ራሱንም ታላቅ ያደርግ ነበር።
[10] ከታናናሾቹም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኀይል ይህ ነው ” እያሉ ሁሉም ያደምጡት ነበር።
[11] ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላው ያታልላቸው ስለ ነበር ያዳምጡት ነበር።
[12] ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብኮላቸው በአመኑ ጊዜ ሴቶችም ወንዶችም ተጠመቁ።
[13] ሲሞንም ወዲያውኑ አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ይከተል ጀመር፤ በፊልጶስም እጅ የሚደረገውን ተአምርና ታላቅ ኀይል ባየ ጊዜ ይደነቅ ነበር።
[14] በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትም የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኩላቸው።
[15] ወርደውም መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጸለዩላቸው።
[16] በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ እንጂ ከመካከላቸው በአንዱ ላይ ስንኳ መንፈስ ቅዱስ ገና አልወረደም ነበርና።
[17] በዚያ ጊዜም እጃቸውን ጫኑባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ።
[18] ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በጫኑበት ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድ ባየ ጊዜ ገንዘብ አመጣላቸውና፥
[19] “እጄን በምጭንበት ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ዘንድ ለእኔም ይህን ሥልጣን ስጡኝ ” አላቸው።
[20] ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው ፥ “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ልትገዛ ዐስበሃልና ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።
[21] በዚህ ነገር ዕድልና ርስት የለህም፥ በእግዚአብሔር ፊት ልብህ የቀና አይደለምና።
[22] አሁንም ከክፋትህ ተመለስና ንስሓ ግባ። የልቡናህንም ዐሳብ ይተውልህ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ለምን።
[23] በመራራ መርዝ ተመርዘህ፥ በዐመፃ ማሰሪያ ተተብትበህ የምትኖር ሆነህ አይሃለሁና።”
[24] ሲሞንም መልሶ ፥ “ካላችሁት ሁሉ ምንም እንዳይደርስብኝ እናንተ ወደ እግዚአብሔር ለምኑልኝ ” አለ።
[25] እነርሱም ከመሰከሩና የእግዚአብሔርን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በብዙዎች የሰማርያ መንደሮችም የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ።
[26] የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን ተናገረው፤ እንዲህም አለው ፥ “በቀትር ጊዜ ተነሣና በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ።”
[27] ተነሥቶም ሄደ፤ እነሆም፥ የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ ጃንደረባ ከሹሞችዋ የበለጠ፥ በሀብቷም ሁሉ ላይ በጅሮንድ የነበረ፥ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ነበር፤ እርሱም ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
[28] ሲመለስም በሰረገላው ላይ ተቀምጦ የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።
[29] መንፈስ ቅዱስም ፊልጶስን ፥ “ሂድ፤ ይህን ሰረገላ ተከተለው ” አለው።
[30] ፊልጶስም ፈጥኖ ደርሶ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማው፤ ፊልጶስም ፥ “በውኑ የምታነበውን ታውቀዋለህን?” አለው።
[31] ጃንደረባውም ፥ “ያስተማረኝ ሳይኖር በምን አውቀዋለሁ?” አለው፤ ወደ ሰረገላውም ወጥቶ አብሮት ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።
[32] ያነበው የነበረ የመጽሐፉ ቃልም እንዲህ የሚል ነበር፤ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
[33] በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዶአልና ትውልዱን ማን ይናገራል?”
[34] ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ ፥ “ነቢዩ ስለ ማን እንዲህ ይላል? ስለ ራሱ ነውን? ወይስ ስለ ሌላ? እባክህ ንገረኝ ” አለው።
[35] ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ስለ ኢየሱስም ከዚያው መጽሐፍ ጀምሮ አስተማረው።
[36] በመንገድ ሲሄዱም ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም ፥ “እነሆ፥ ውኃ፥ መጠመቅን ምን ይከለክለኛል?” አለው።
[37] ፊልጶስም ፥ “በፍጹም ልብህ ብታምን ይገባሃል ” አለው፤ ጃንደረባውም መልሶ ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እኔ አምናለሁ ” አለው።
[38] ሰረገላውንም እንዲያቆሙ አዘዘ፤ አቁመውም ፊልጶስና ጃንደረባው በአንድነት ወደ ውኃው ወረዱ፤ አጠመቀውም።
[39] ከውኃዉም ከወጡ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባዉም ከዚያ ወዲያ አላየውም፤ ደስ እያለውም መንገዱን ሄደ።
[40] ፊልጶስም አዛጦን ወደምትባል ሀገር ደረሰ፤ በከተማዎችም ሁሉ እየተዘዋወረ ወደ ቂሳርያ እስኪደርስ ድረስ ያስተምር ነበር።