[1] አንፊጶልና አጶሎንያ ወደሚባሉ ሀገሮችም ሄዱ፤ የአይሁድ ምኵuራብ ወደ አለበት ወደ ተሰሎንቄም ደረሱ።
[2] ጳውሎስም እንደ አስለመደው ወደ እነርሱ ገብቶ ሦስት ሳምንት ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ሲከራከራቸው ሰነበተ።
[3] ክርስቶስ እንዲሞት ከሙታንም ተለይቶ እንዲነሣ፥ እየተረጐመና እየአስተማራቸው፥ “ይህ እኔ የነገርኋችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ” ይል ነበር።
[4] ከእነርሱና ከደጋጎች አረማውያንም ብዙ ሰዎች፥ ከታላላቆች ሴቶችም ጥቂቶች ያይደሉ አምነው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ሆኑ።
[5] የማያምኑ አይሁድ ግን ቀኑባቸው፤ ከገበያም ክፉዎች ሰዎችን አምጥተው፥ ሰዎችንም ሰብስበው ሀገሪቱን አወኳት፤ ፈለጓቸውም፤ የኢያሶንን ቤትም በረበሩ፤ ወደ ሕዝቡም ሊያወጧቸው ሽተው ነበር።
[6] በአጧቸውም ጊዜ ኢያሶንን ጐተቱት፤ በዚያም የነበሩትን ጓደኟች ጭምር ወደ ሹሞቹ ወሰዱአቸው፤ እየጮኹም እንዲህ ይሉ ነበር ፥ “ዓለምን የሚያውኳት እነዚህ ናቸው፤ ወደዚህም መጥተዋል።
[7] ይህ ኢያሶንም ተቀበላቸው፤ እነርሱም በቄሣር ላይ የወንጀል ሥራ ይሠራሉ፤ ሌላ ሕግንም ያስተምራሉ፤ ኢየሱስም ሌላ ንጉሥ ነው ” ይላሉ።
[8] ሕዝቡና የከተማው ሹሞችም ይህን በሰሙ ጊዜ ታወኩ።
[9] ከኢያሶንና ከጓደኟቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው።
[10] ወንድሞች ግን ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሸኙአቸው፤ ወደዚያም በደረሱ ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵuራብ ገቡ።
[11] በተሰሎንቄ ካሉትም እነርሱ ይሻላሉ፤ በፍጹም ደስታ ቃላቸውን ተቀብለዋልና፤ ነገሩም እንደ አስተማሩአቸው እንደ ሆነ ለመረዳት ዘወትር መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር።
[12] ከመካከላቸውም ያመኑ ብዙዎች ነበሩ፤ ከአረማውያን ወገን የሆኑ ብዙ ደጋግ ሴቶችም ነበሩ፤ ወንዶችም ብዙዎች ነበሩ።
[13] በተሰሎንቄ የነበሩ አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ አስተማረ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አወኩአቸው።
[14] ያንጊዜም ወንድሞች ጳውሎስን ሸኝተው ወደ ባሕር አደረሱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን በዚያው ቀሩ።
[15] ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴና ከተማ ድረስ አብረውት መጥተው ነበርና ፈጥነው ይከተሉት ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ላካቸው፤ ተመልሰውም ሄዱ።
[16] ጳውሎስም በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ከተማው ሁሉ ጣዖት ሲያመልኩ ባየ ጊዜ ልቡናው ተበሳጨ።
[17] ስለዚህም በምኵuራብ አይሁድንና እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ሁልጊዜም በገበያ የሚያገኛቸውን ሁሉ ይከራከራቸው ነበር።
[18] የኤፌቆሮስን ትምህርት ከተማሩ ፈላስፋዎች መካከልና ረዋቅያውያን ከሚባሉት ወገን የሆኑ ሌሎች ፈላስፎችም የተከራከሩት ነበሩ፤ እኩሌቶችም ፥ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎችም ፥ “ስለ ኢየሱስ ከሙታን ስለ መነሣቱም ሰብኮላቸዋልና የአዲስ አምላክ ትምህርትን ያስተምራል ” አሉ።
[19] ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደሚባል ሸንጎ ወሰዱት፤ እንዲህም አሉት ፥ “ይህን የምታስተምረውን አዲስ ትምህርት እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? እስቲ ንገረን?
[20] በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና እኛም ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ልንረዳ እንወዳለን።”
[21] የአቴና ሰዎችና በዚያም የነበሩ እንግዶች ሁሉ አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር ሌላ ዐሳብ አልነበራቸውም።
[22] ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ ውስጥ ቆሞ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ የአቴና ሰዎች! በሥራችሁ ሁሉ አማልክትን ማምለክ እንደምታበዙ አያችኋለሁ።
[23] በዚህም ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን የምታመልኩበትን መሠዊያችሁን አየሁ፤ እነሆ፥ እኔ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ።
[24] ዓለሙንና በእርሱም ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም።
[25] እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን፥ ሌላውንም ነገር ሁሉ ለሁሉ ይሰጣልና እንደ ችግረኛ የሰው እጅ አያገለግለውም።
[26] እርሱም በምድር ሁሉ ላይ ይኖሩ ዘንድ ሰዎችን ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ ይኖሩባትም ዘንድ ዘመንንና ቦታን ወስኖ ሠራላቸው።
[27] ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉት ዘንድ፤ ነገር ግን ከሁላችን የራቀ አይደለም።
[28] እኛ በእርሱ ሕይወትን እናገኛለን፤ በእርሱም እንንቀሳቀሳለን፤ በእርሱም ጸንተን እንኖራለን፤ ከመካከላችሁም ፥ ‘እኛ ዘመዶቹ ነን ’ የሚሉ ፈላስፎች አሉ።
[29] እንግዲህ እኛ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆን በሰው ዕውቀትና ብልሀት በተቀረጸ በድንጋይና በብር፥ በወርቅም አምላክነቱን ልንመስለው አይገባም።
[30] የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፤ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሓ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዞአል።
[31] በመረጠው ሰው እጅ በዓለም በእውነት የሚፈርድባትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱን ከሙታን ለይቶ በማስነሣቱም ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት መልሶአልና።”
[32] የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኩሌቶቹ አፌዙበት፤ ሌሎችም ፥ “ስለዚህ ነገር በሌላ ቀን እናዳምጥሃለን ” አሉት።
[33] ጳውሎስም ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ።
[34] አምነው የተከተሉት ሰዎችም ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ከአርዮስፋጎስ ባለሥልጣኖች ወገን የሚሆን ዲዮናስዮስ ነበር፤ ደማሪስ የምትባል ሴትም ነበረች፤ ሌሎችም አብረዋቸው ነበሩ።