Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:52

[1] ከእነርሱም ከተለየን በኋላ እኛ በመርከብ ተሳፍረን፥ መንገዳችንንም አቅንተን ወደ ቆስ መጣን፤ በበነጋውም ወደ ሮዶስ፥ ከዚያም ወደ ጳጥራ ገባን።

[2] ወደ ፊንቄም የሚያልፍ መርከብ አግኝተን በዚያ ላይ ተሳፍረን ሄድን።

[3] ቆጵሮስንም አየናት፤ በስተ ግራችንም ትተናት ወደ ሶርያ ሄድን፤ ወደ ጢሮስም ወረድን፤ በመርከብ ያለውን ጭነት ሁሉ በዚያ ያራግፉ ነበርና።

[4] በዚያም ደቀ መዛሙርትን አገኘንና በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተገልጿላቸው ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ነገሩት።

[5] ከዚህም በኋላ ለመሄድ ወጣን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን።

[6] እርስ በርሳችንም ተሳስመን ተሰነባበትን፤ ከዚህም በኋላ ወደ መርከብ ወጣን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

[7] እኛም ከጢሮስ ወጥተን አካ ወደምትባል ሀገር መጣን፤ ወንድሞቻችንንም አግኝተን ሰላም አልናቸው፤ በእነርሱም ዘንድ አንድ ቀን አደርን።

[8] በማግሥቱም ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ ወደ ወንጌላዊው ወደ ፊልጶስ ቤትም ገባን፤ እርሱም ከሰባቱ ወንድሞች ዲያቆናት አንዱ ነው።

[9] ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።

[10] በእርሱም ዘንድ ብዙ ቀን ኖርን፤ ከይሁዳም አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ወረደ።

[11] ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ እጁንና እግሩን በገዛ እጁ አስሮ እንዲህ አለ ፥ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ የዚህን መታጠቂያ ጌታ አይሁድ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።”

[12] ይህንም ሰምተን የሀገሪቱን ሰዎች ይዘን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ጳውሎስን ማለድነው።

[13] ጳውሎስ ግን መልሶ ፥ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና እግር ብረትን ብቻ አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም ቢሆን የቈረጥሁ ነኝ ” አለ።

[14] እንቢ ባለ ጊዜም ዝም አልን፤ እኛም እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን ብለን ተውነው።

[15] ከእነዚያም ቀኖች በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።

[16] ከደቀ መዛሙርትም ከቂሳርያ አብረውን የመጡ ነበሩ፤ ሄደንም ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ወገን ከሆነው በቆጵሮስ በሚኖረው በምናሶን ቤት አደርን።

[17] ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜም ወንድሞቻችን በደስታ ተቀበሉን።

[18] በማግሥቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ገባ፤ ቀሳውስትም ሁሉ በዚያ ነበሩ።

[19] ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ሐዋርያነት እግዚአብሔር በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ነገራቸው።

[20] እነርሱም ሰምተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ ፥ “ወንድማችን ሆይ፥ ከአይሁድ መካከል ያመኑት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህን? ሁሉም ለኦሪት የሚቀኑ ናቸው።

[21] ነገር ግን የማይሆነውን እንደምታስተምር፥ የሙሴንም ሕግ እንደምታስተዋቸው፥ በአሕዛብ መካከል ያሉ ያመኑ አይሁድንም ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፥ የኦሪትንም ሕግ እንዳይፈጽሙ እንደምትከለክላቸው ስለ አንተ ነግረዋቸዋል።

[22] አሁንሳ ምን ይሁን? ሕዝቡ ወደዚህ እንደ መጣህ ይሰሙና ይሰበሰቡ ይሆናል።

[23] ስለዚህም ይህን የምልህን አድርግ ፥ ብፅዐት ያላቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ።

[24] ይዘሃቸው ሂድ፤ ከእነርሱም ጋር ራስህን አንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ስለ እነርሱ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ የሚያሙህም በሐሰት እንደ ሆነ፥ አንተም የኦሪትን ሕግ እንደምትጠብቅ ሁሉም ያውቃሉ።

[25] ስለሚአምኑት አሕዛብ ግን እርም ከሆነውና ለጣዖታት ከሚሠዉት፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደምን ከመብላት እንዲከለከሉ እኛ አዝዘናል።”

[26] ያንጊዜም ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር ነጻ። የመንጻታቸውንም ወራት መድረሱን ከነገራቸው በኋላ ሁሉም እየአንዳንዳቸው መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞአቸው ገባ።

[27] በሰባተኛውም ቀን ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በመቅደስ አዩት፤ ሕዝቡንም ሁሉ በእርሱ ላይ አነሳሥተው ያዙት።

[28] እየጮሁም እንዲህ አሉ ፥ “እናንተ የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ ርዱን፤ በየስፍራው ሕዝባችንን፥ ኦሪትንም፥ ይህንም ስፍራ የሚቃወም ትምህርት ለሰው ሁሉ የሚያስተምር እነሆ፥ ይህ ሰው ነው፤ አሁንም አረማውያንን ወደ መቅደስ አስገባ፤ ቤተ መቅደስንም አረከሰ።

[29] የኤፌሶን ሀገር ሰው የሆነ ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና፤ ጳውሎስም ወደ ቤተ መቅደስ ያስገባው መስሎአቸው ነበርና።

[30] ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ሄደው ጳውሎስን ጐትተው ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ በሩንም ሁሉ ዘጉ።

[31] ሊገድሉትም ፈልገው ብዙ ደበደቡት፤ ወዲያውም ኢየሩሳሌም በመላዋ እንደ ታወከች የሚገልጥ መልእክት ወደ ሻለቃው ደረሰለት።

[32] በዚያ ጊዜም ጭፍሮቹን ከአለቆቻቸው ጋር ይዞ ወደ እነርሱ ሄደ፤ እነርሱም የሻለቃውን ጭፍሮች ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታታቸውን ተዉ።

[33] የሻለቃውም ቀረብ ብሎ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር አዘዘ፤ “ምንድነው? ምንስ አደረገ?” ብሎም ጠየቀ።

[34] ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ ነው፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አይደለም እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ሻለቃውም ሕዝቡ የሚታወክበትን ርግጡን ማወቅ ተሣነው፤ ወደ ወታደሮቹም ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ።

[35] ደረጃውንም በሚወጣበት ጊዜ ወታደሮች ተሸክመው አወጡት፤ ሰው ይጋፋ ነበርና።

[36] ብዙዎችም ይከተሉት ነበር፤ ሕዝቡም ፥ “አስወግዱት ” እያሉ ይጮሁ ነበር።

[37] ወደ ሰፈርም በደረሰ ጊዜ ጳውሎስ ሻለቃውን ፥ “ላነጋግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው፤ ሻለቃውም ፥ “የጽርዕ ቌንቌ ታውቃለህን?” አለው።

[38] “ምናልባት ከዚህ በፊት ወንጀል የሠራህና ከነፍሰ ገዳዮች አራት ሺህ ሰዎችን ይዘህ ወደ ምድረ በዳ የወጣህ ያ ግብፃዊ አንተ አይደለህምን?” አለው።

[39] ጳውሎስም ፥ “እኔስ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የተወለድሁባትም ሀገር ጠርሴስ የታወቀች የቂልቅያ ከተማ ናት፤ ለሕዝቡም እንድነግራቸው ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ ” አለው።

[40] በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ እጁን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ ጳውሎስ በዕብራይስጥ ቌንቌ ተናገረ፤ እንዲህም አለ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters