Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:34

[1] ሐናንያ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም ሰጲራ ትባል ነበር፤ መሬቱንም ሸጠ።

[2] ከሚስቱም ጋራ ተማክሮ የዋጋዉን እኩሌታ አስቀረ፤ የዋጋውንም እኩሌታ አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አስቀመጠ።

[3] ጴጥሮስም ፥ “ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልለው ዘንድ፥ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ?

[4] ጥንቱን ሳትሸጠው ያንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በፈቃድህ አልነበረምን? ይህን ነገር በልብህ ለምን ዐሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አላታለልህም ” አለው።

[5] ሐናንያም ይህን በሰማ ጊዜ ወድቆ ሞተ፤ ጽኑ ፍርሀትም ሆነ፤ የሰሙትም ሁሉ ፈሩ።

[6] ከእነርሱም ጐልማሶች ተነሥተው ገነዙት፤ ተሸክመውም ወስደው ቀበሩት።

[7] ይህም ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላ ሚስቱ መጣች፤ ባልዋም የሆነውን ሳታውቅ ገባች።

[8] ጴጥሮስም ፥ “እስኪ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን የሸጣችሁት ይህን ለሚያህል ነውን?” አላት፤ እርስዋም ፥ “አዎን፥ እንዲሁ ነው ” አለች።

[9] ጴጥሮስም ፥ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንፈስ ትፈታተኑት ዘንድ እንዴት ተባበራችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግሮች በበር ናቸው፤ አንቺንም ይወስዱሻል ” አላት።

[10] ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወድቃ ሞተች፤ ጐልማሶችም በገቡ ጊዜ በድንዋን አገኙ፤ ወስደውም በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት።

[11] በአብያተ ክርስቲያናትና ይህንም ነገር በሰሙት ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ሆነ።

[12] በሐዋርያት እጅም በሕዝቡ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤ በቤተ መቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ነበሩ።

[13] ሕዝቡም እጅግ ያከብሩአቸው ነበረ። ከሌሎችም ይቀርባቸው ዘንድ አንድ ስንኳን የሚደፍር አልነበረም።

[14] በጌታችንም የሚያምኑ ብዙዎች ይጨመሩ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙዎች ነበሩ።

[15] ጴጥሮስም አልፎ ሲሄድ ጥላው ያርፍባቸው ዘንድ ድውዮችን በአልጋና በቃሬዛ እያመጡ በአደባባይ ያስቀምጡአቸው ነበር፤

[16] ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከአሉ ከተሞች ብዙዎች ይመጡ ነበር፤ የታመሙትንና ክፉዎች አጋንንት የያዙአቸውንም ያመጡ ነበር፥ ሁሉም ይፈወሱ ነበር።

[17] ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገኖችም ቀንተው በእነርሱ ላይ ተነሡ።

[18] እጃቸውንም በሐዋርያት ላይ አነሡ፤ ያዙአቸውም፤ በሕዝቡ ወኅኒ ቤትም አስገቧቸው።

[19] የእግዚአብሔር መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒ ቤቱን ደጃፍ ከፍቶ አወጣቸው፤ እንዲህም አላቸው።

[20] “ሂዱ፤ ወደ ቤተ መቅደስም ግቡና ለሕዝብ ይህን የሕይወት ቃል አስተምሩአቸው።”

[21] ይህንም በሰሙ ጊዜ ጥዋት ገስግሠው ወደ ቤተ መቅደስ ገቡና አስተማሩ፤ ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ግን ጉባኤውንና ከእስራኤልም ቤት ሽማግሌዎችን ሁሉ ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም ያመጡአቸው ዘንድ ወደ ወኅኒ ቤት ላኩ።

[22] አሽከሮቻቸውም መጥተው በወኅኒ ቤት አጡአቸውና ተመልሰው ነገሩአቸው።

[23] “ወኅኒ ቤቱንም ዙሪያውን ተዘግቶ በቐልፍም ተቈልፎ አገኘነው፤ ወታደሮቹም በሩን ይጠብቁ ነበር፤ ነገር ግን ከፍተን በገባን ጊዜ በውስጥ ያገኘነው የለም ” አሉአቸው።

[24] ሊቃነ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ሹምም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ፥ የሚያደርጉትን አጥተው ፥ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” አሉ።

[25] አንድ ሰውም መጥቶ ፥ “ያሰራችኋቸው እነዚያ ሰዎች እነሆ፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ ናቸው፤ ቆመውም ሕዝቡን ያስተምራሉ ” ብሎ ነገራቸው።

[26] ከዚህም በኋላ የቤተ መቅደሱ ሹም ከሎሌዎቹ ጋር ሔዶ አባብሎ አመጣቸው፤ በግድም አይደለም፤ በድንጋይ እንዳይደበድቧቸው ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና።

[27] አምጥተውም በሸንጎ መካከል አቆሙአቸው፤ ሊቀ ካህናቱም መረመራቸው፤

[28] “በኢየሱስ ስም ለማንም እንዳታስተምሩ ከልክለናችሁ አልነበረምን? እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ላይ ታመጡብን ዘንድ ትሻላችሁን?” አላቸው።

[29] ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉአቸው ፥ “ለሰው ከመታዘዝ ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባል።

[30] የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ ክዳችሁ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን አስነሣው።

[31] እግዚአብሔር እርሱን ለእስራኤል ንስሓን፥ የኀጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ ራስም አዳኝም አደረገው፤ በቀኙም አስቀመጠው።

[32] እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮቹ ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።”

[33] ይህንም በሰሙ ጊዜ ተበሳጩ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩ፤ ሊገድሉአቸውም ወደዱ።

[34] በሸንጎዉም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ የኦሪት መምህር ስሙን ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ ተነሣ፤ ሐዋርያትንም ከጉባኤዉ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ።

[35] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

[36] ቀድሞም ከዚህ ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፤ ነገር ግን እርሱም ጠፋ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፤ እንደ ኢምንትም ሆኑ።

[37] ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ እርሱም ሞተ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ።

[38] አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ሰዎች ራቁ፤ ተዉአቸውም፤ ይህ ምክራቸው፥ ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል ይጠፋልም።

[39] ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት አትችሉም፤ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።”

[40] እሺም አሰኛቸው፤ ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፉአቸው፤ እንግዲህ ወዲህም በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ገሥጸው ተዉአቸው።

[41] እነርሱም ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ስለ ስሙ መከራ ይቀበሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አድሎአቸዋልና።

[42] ሁልጊዜም በቤተ መቅደስና በቤት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አልተዉም።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters