Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:43

[1] ከይሁዳ ሀገርም የወረዱ ሰዎች ፥ “እንደ ሙሴ ሕግ ካልተገዘራችሁ ልትድኑ አትችሉም ” እያሉ ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር።

[2] ሕዝቡም እጅግ ታወኩ፤ ጳውሎስንና በርናባስንም ተከራከሩአቸው፤ ስለዚህ ነገርም ጳውሎስንና በርናባስን፥ ጓደኟቻቸውንም በኢየሩሳሌም ወደ አሉት ወደ ሐዋርያትና ቀሳውስት ሊልኳቸው ተማከሩ።

[3] ከቤተ ክርስቲያንም በተላኩ ጊዜ ወደ ሰማርያና ወደ ፊንቄ ደርሰው አሕዛብ ወደ ሃይማኖት እንደ ተመለሱ ነገሩቸአቸው፤ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው።

[4] ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም ምእመናንና ሐዋርያት፥ ቀሳውስትም ተቀበሉአቸው፤ እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ያደረገላቸውን ነገሩአቸው።

[5] ነገር ግን ካመኑት ከፈሪሳውያን ወገን አንዳንዶች ተነሥተው ፥ “ትገዝሩአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዝዙአቸው ዘንድ ይገባል ” አሉ።

[6] ሐዋርያትና ቀሳውስትም ስለዚህ ነገር የሚያደርጉትን ያዩ ዘንድ ተሰበሰቡ።

[7] ብዙ ክርክርም ከተከራከሩ በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ፥ “ወንድሞች ሆይ፥ ስሙ፤ ለአሕዛብ ከአፌ የወንጌሉን ቃል እንዳሰማቸውና እንዲያምኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ መረጠኝ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

[8] ልብን የሚያውቅ እግዚአብሔርም ለእኛ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው።

[9] ልባቸውንም በእምነት አንጽቶ ከእኛ አልለያቸውም።

[10] አሁንም እግዚአብሔርን አትፈታተኑት፤ እኛም አባቶቻችንም ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ ለምን ትጭናላችሁ?

[11] ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንድን ዘንድ እንታመናለን፤ እነርሱም እንደ እኛ ይድናሉ።”

[12] ያንጊዜም ሕዝቡ ሁሉ ጸጥ ብለው እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያደረገላቸውን ተአምራትና ድንቅ ሥራ ሁሉ ሲናገሩ ጳውሎስንና በርናባስን አዳመጡአቸው።

[13] እነርሱም ጸጥ ባሉ ጊዜ ያዕቆብ መልሶ እንዲህ አለ ፥ “ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ።

[14] ስምዖንም፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ አሕዛብን ይቅር እንዳላቸውና ከውስጣቸውም ለስሙ ሕዝብን እንደ መረጠ ተናግሮአል።

[15] በዚህም መጽሐፍ እንዲህ ብሎ እንደ ተናገረ የነቢያት ቃል ይስማማል።

[16] ከዚህም በኋላ የወደቀችውን የዳዊትን ቤት መልሼ እሠራታለሁ፤ ፍራሽዋንም አድሳለሁ፤

[17] የቀሩት ሰዎችና ስሜም የተጠራባቸው አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር፤

[18] ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።

[19] “አሁንም ወደ እግዚአብሔር በተመለሱ አሕዛብ ላይ ሥርዐት አታክብዱ እላችኋለሁ።

[20] ነገር ግን ለጣዖት ከሚሠዋው፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደም ከመብላት እንዲርቁ፥ ለራሳቸው የሚጠሉትንም በወንድሞቻቸው ላይ እንዳያደርጉ እዘዙአቸው።

[21] ሙሴም ከጥንት ጀምሮ በየከተማዉ የሚሰብክላቸው ትምህርት ነበር፤ በየምኵuራቡም በየሰንበቱ ያነብቡት ነበር።”

[22] ከዚህም በኋላ ሐዋርያትና ቀሳውስት ሕዝቡም ሁሉ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጿኪያ የሚልኳቸውን ሰዎች ይመርጡ ዘንድ ተስማሙ፤ ከባልንጀሮቻቸው መካከልም የተማሩትን ሰዎች በርናባስ የተባለ ይሁዳንና ሲላስን መረጡ።

[23] እንዲህ የምትል መልእክትም በእጃቸው ጻፉ፤ “ከሐዋርያትና ከቀሳውስት ከወንድሞችም በአንጿኪያ፥ በሶርያና በኪልቅያ ለሚኖሩ፥ ከአሕዛብ ላመኑ ወንድሞቻችን ትድረስ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ ደስ ይበላችሁ።

[24] ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ፥ ‘ትገዘሩ ዘንድና የኦሪትንም ሕግ ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል ’ ብለው በነገር እንደ አወኩአችሁና ልባችሁን እንደ አናወጡት ሰምተናል።

[25] ሁላችን ከተሰበሰብን በኋላ በአንድ ቃል በየን፤ አንድ ሆነንም ከወንድሞቻችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ እናንተ የምንልካቸውን ሰዎች መረጥን።

[26] እነርሱም ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡ ሰዎች ናቸው።

[27] ይሁዳንና ሲላስን ልከናቸዋልና እነርሱ በቃላቸው ይህን ያስረዱአችኋል።

[28] ሥርዐት እንዳናከብድ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነውና፤ ነገር ግን ይህን በግድ ትተዉ ዘንድ እናዝዛችኋለን።

[29] ለአማልክት የተሠዋውን፥ ሞቶ የተገኘውን፥ ደምንም አትብሉ፤ ከዝሙትም ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ፥ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ፤ ደኅና ሁኑ።”

[30] እነርሱም ተልከው ወደ አንጿኪያ ወረዱ፤ ሕዝቡንም ሰብስበው የተላከውን ደብዳቤ ሰጡአቸው።

[31] እነርሱም አንብበው እጅግ ደስ አላቸው፥ ተጽናኑም።

[32] ይሁዳና ሲላስም መምህራን ነበሩና አስተማሩአቸው፤ ወንድሞችንም በብዙ ቃል አጽናኑአቸው።

[33] በእነርሱም ዘንድ አያሌ ቀን ከተቀመጡ በኋላ ወንድሞቻቸውን ተሰናብተው በሰላም ወደ ሐዋርያት ተመለሱ።

[34] ሲላስ ግን በዚያ ሊቈይ ወደደ።

[35] ጳውሎስና በርናባስም በአንጿኪያ ቈዩ፤ ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋርም የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አስተማሩም።

[36] ከጥቂት ቀን በኋላም ጳውሎስ በርናባስን ፥ “እንግዲህስ እንመለስና የእግዚአብሔርን ቃል ባስተማርንባቸው ሀገሮች ያሉትን ወንድሞች እንጐብኛቸው፤ እንዴት እንዳሉም እንወቅ ” አለው።

[37] በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ከእነርሱ ጋር ይዞት ሊሄድ ወደደ።

[38] ጳውሎስ ግን ከእነርሱ ጋር ሊወስደው አልፈቀደም፤ እነርሱ በጵንፍልያ ሳሉ ትቶአቸው ሄዶአልና፤ አብሮአቸውም ለሥራ አልመጣም ነበርና።

[39] ስለዚህም ተኰራርፈው እርስ በርሳቸው ተለያዩ፤ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።

[40] ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞችም ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ ሄደ።

[41] በሶርያና በኪልቅያም እየዞረ አብያተ ክርስቲያናትን አጽናና።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters