Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:37

[1] ሕዝቡንም ሲያስተምሩ ሊቃነ ካህናትና የቤተ መቅደስ ሹም፥ ሰዱቃውያንም መጡ።

[2] ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስም የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ በእነርሱ ተናደዱ።

[3] እጃቸውንም ዘርግተው ያዙአቸው፤ ጊዜዉም ፈጽሞ መሽቶ ነበርና እስከ ማግሥቱ ድረስ በወኅኒ ቤት አገቡአቸው።

[4] ቃሉንም ሰምተው ያመኑ ብዙ ሰዎች ናቸው፤ ያመኑት ወንዶች ቐጥርም አምስት ሺህ ያህል ሆነ።

[5] በማግሥቱም አለቆቻቸውና ሽማግሎች፥ ጻፎችም በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።

[6] ሊቀ ካህናቱ ሐና፥ ቀያፋም፥ ዮሐንስና እለእስክንድሮስም፥ የሊቀ ካህናቱም ወገን ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነበሩ።

[7] በአደባባይም አቆሙና ፥ “እናንተ ይህን በማን ስምና በማን ኀይል አደረጋችሁት?” ብለው መረመሩአቸው።

[8] ያንጊዜም በጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና እንዲህ አላቸው ፥ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች ሆይ፥ ስሙ፤

[9] ዛሬ ለበሽተኛው በተደረገው ረድኤት ምክንያት በእናንተ ዘንድ እኛ የሚፈረድብን ከሆነ እንግዲያ ይህ ሰው በምን ዳነ?

[10] እንግዲህ እናንተ ሁላችሁ፥ የእስራኤልም ወገን ሁሉ፥ እናንተ በሰቀላችሁት፥ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ በአስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ሰው እንደ ዳነና በፊታችሁም እንደ ቆመ በርግጥ ዕወቁ።

[11] ይህ እናንተ ግንበኟች የናቃችሁት ድንጋይ ነውና፤ እርሱም የማዕዘን ራስ ሆነ።

[12] መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና።”

[13] ጴጥሮስና ዮሐንስም ግልጥ አድርገው ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፥ ያልተማሩና መጽሐፍን የማያውቁ ሰዎች እንደ ሆኑ ዐውቀው አደነቁ፤ ሁልጊዜም ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ ዐወቁ።

[14] ያን የዳነውን ሰውም ከእነርሱ ጋር ቆሞ በአዩት ጊዜ የሚሉትን አጡ።

[15] ከሸንጎውም ጥቂት ፈቀቅ አደረጉአቸውና እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።

[16] እንዲህም አሉ ፥ “እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? እነሆ፥ በእነርሱ የሚደረገው ተአምር በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ዘንድ ታወቀ፤ ግልጥም ሆነ፤ ልንሰውረውም አንችልም።

[17] ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ እጅግ እንዳይስፋፋ ዳግመኛ በኢየሱስ ስም ሰውን እንዳያስተምሩ አጠንክረን እንገሥጻቸው።”

[18] ጠርተውም ፥ “ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ አትናገሩ አታስተምሩም ” ብለው አዘዙአቸው።

[19] ጴጥሮስና ዮሐንስም እንዲህ ብለው መለሱላቸው ፥ “እግዚአብሔርን ያይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ።

[20] እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም።”

[21] እነርሱንም የሚቀጡበት ምክንያት ስለ አጡባቸው ገሥጸው ለቀቁአቸው፤ ስለ ተደረገው ተአምር ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበርና።

[22] ይህ የድኅነት ምልክት ለተደረገለት ለዚያ ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበረና።

[23] ተፈትተውም ወደ ሰዎቻቸው ሄዱ፤ ሊቃነ ካህናትና ሽማግሌዎችም ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው።

[24] ይህንም በሰሙ ጊዜ በአንድነት ቃላቸውን ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ ፥ “ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠርህ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፥

[25] አንተ ራስህ በአባታችን በባሪያህ በዳዊት አፍ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብለህ የተናገርህ ፥ አሕዛብ ለምን ተሰበሰቡ? ሕዝቡስ ለምን ከንቱ ነገርን ተናገሩ?

[26] የምድር ነገሥታት ለምን ተነሡ? አለቆችስ ከእነርሱ ጋር አብረው በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ ለምን ዶለቱ?

[27] በቀባኸው በቅዱስ ልጅህ ላይ ሄሮድስና ጰንጤናዊው ጲላጦስ ከወገኖቻቸውና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በእውነት በዚች ሀገር ላይ ዶለቱ።

[28] እጅህና ምክርህ እንዲደረግ የወሰኑትን ይፈጽሙ ዘንድ።

[29] አሁንም አቤቱ፥ ትምክህታቸውን ተመልከት፤ ቃልህንም በግልጥ ያስተምሩ ዘንድ ለባሮችህ ስጣቸው።

[30] በቅዱሱ ልጅህም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕሙማንን ትፈውስ ዘንድ ተአምራትንና ድንቅ ሥራንም ታደርግ ዘንድ እጅህን ዘርጋ።”

[31] ሲጸልዩም በአንድነት ተሰብስበው የነበሩበት ቦታ ተናወጠ፤ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላባቸውና የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥ አስተማሩ።

[32] ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ “ይህ የእኔ ገንዘብ ነው ” የሚል አልነበረም።

[33] ሐዋርያትም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኀይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሕዝቡም ዘንድ ታላቅ ጸጋ ነበራቸው።

[34] ከእነርሱም አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረም፤ ቤትና መሬት ያላቸውም ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር።

[35] አምጥተውም በሐዋርያት እግር አጠገብ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ ይከፍሉት ነበር።

[36] በሐዋርያትም ዘንድ ትርጓሜዉ የመጽናናት ልጅ የሚሆን በርናባስ የተባለ የሌዊ ወገን ስሙን ዮሴፍ የሚሉት አንድ የቆጵሮስ ሰው ነበር።

[37] እርሻም ነበረውና ሽጦ ገንዘቡን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters