[1] በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት።
[2] ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤
[3] “ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስትመሰገን አግኝተናታል።
[4] ነገር ግን ነገር እንዳላበዛብህ በአጭሩ ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
[5] ይህን ሰው ሲሳደብና ወንጀል ሲሠራ፥ አይሁድንም ሁሉ በየሀገሩ ሲያውክ፥ ናዝራውያን የተባሉት ወገኖች የሚያስተምሩትንም ክህደት ሲያስተምር አግኝተነዋል።
[6] ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም ልንፈርድበት ፈልገን ነበር።
[7] ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ጭንቅ ከእጃችን ነጥቆ ወደ አንተ ላከው።
[8] ከሳሾቹንም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዛቸው፤ የከሰስንበትንም ነገር ሁሉ መርምረህ ከእርሱ ልትረዳ ትችላለህ።”
[9] አይሁድም ፥ “እውነት ነው፤ እንዲሁ ነው ” ብለው መለሱ።
[10] ሀገረ ገዢውም እንዲናገር ጳውሎስን ጠቀሰው፤ ጳውሎስም እንዲህ አለ ፥ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ አስተዳዳሪ እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ጠባያቸውንም ታውቃለህ። አሁንም ደስ እያለኝ ክርክሬን አቀርባለሁ።
[11] እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይሆን ልታውቀው ትችላለህ፤
[12] በምኵuራብ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ቢሆን፥ በከተማም ቢሆን ሕዝብን ሳውክ፥ ከማንም ጋር ስከራከር አላገኙኝም።
[13] በሚከስሱኝ ሁሉ በፊትህ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም።
[14] ነገር ግን ይህን አረጋግጥልሃለሁ፤ እኔ በሕግ ያለውን፥ በነቢያትም የተጻፈውን ሁሉ አምኜ እነርሱ ክህደት ብለው በሚጠሩት ትምህርት የአባቶቼን አምላክ አመልከዋለሁ።
[15] እነርሱም ለጻድቃንና ለኃጥኣን የሙታን ትንሣኤ ይሆን ዘንድ እንደሚጠብቁ ለእኔም እንዲሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ተስፋ አለኝ።
[16] እንዲሁ እኔም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ የማታወላውል ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እጋደላለሁ።
[17] ከብዙ ዓመታትም በኋላ ለወገኖቼ ምጿትንና መሥዋዕትን ላደርግ መጣሁ።
[18] በዚያም ጊዜ ከእስያ የመጡ አይሁድ ከሕዝብ ጋር በመከራከር፥ ወይም በፍጅት ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ።
[19] አሁንም በእኔ ላይ ነገር ከአላቸው ወደ አንተ ይምጡና ይክሰሱኝ።
[20] ወይም እኔ በሸንጎ ቆሜ ሳለሁ ያገኙብኝ በደል እንደ አለ እነዚህ ራሳቸው ይመስክሩ።
[21] በመካከላቸው ቆሜ ከአስተማርኋት አንዲት ትምህርት በቀር ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም። ‘ሙታን ይነሣሉ ’ በማለቴም ዛሬ በአንተ ዘንድ በእኔ ይፈረድብኛል።”
[22] ፊልክስ ግን አይሁድ ከጥንት ጀምሮ የክርስቲያንን ወገኖች ሕግና ትምህርት እንደሚቃወሙ ያውቅ ነበር፤ ስለዚህም “እንኪያስ የሺ አለቃው ሉስዮስ በመጣ ጊዜ ነገራችሁን እናውቅ ዘንድ እንመረምራለን ” ብሎ ቀጠራቸው።
[23] የመቶ አለቃውንም ጳውሎስን እንዲጠብቀው፥ በሰፊ ቦታም እንዲያኖረው፥ እንዳያጠብበትም፥ ሊያገለግሉት በመጡ ጊዜም ከወዳጆቹ አንዱን ስንኳ እንዳይከለክልበት አዘዘ።
[24] ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ ከአይሁዳዊት ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ። ልኮም ጳውሎስን አስጠራው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ማመንም የሚናገረውን ነገር ሰማው።
[25] እርሱም ስለ ጽድቅና ስለ ንጽሕና፥ ስለሚመጣውም ኵuነኔ በነገራቸው ጊዜ በዚህ የተነሣ ፊልክስ ፈራና ጳውሎስን ፥ “አሁንስ ሂድ፤ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ” አለው።
[26] ፊልክስም እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ የሚሰጠው መስሎት ነበር፤ ስለዚህ ዘወትር ይጠራውና ያነጋግረው ነበር።
[27] ሁለት ዓመትም ካለፈ በኋላ፥ ፊልክስ ተሻረና ጶርቅዮስ ፊስጦስ የሚባል ሌላ ሀገረ ገዢ በእርሱ ቦታ መጣ፤ ፊልክስም በግልጥ ለአይሁድ ሊያዳላ ወደደ፤ ስለዚህም ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።