Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:18

[1] ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ።

[2] ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጿት ይለምን ዘንድ ሁልጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር።

[3] ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጿት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው።

[4] ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተው ፥ “ወደ እኛ ተመልከት ” አለው፤

[5] ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጿት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር።

[6] ጴጥሮስም ፥ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ፥ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ ” አለው።

[7] በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ ያንጊዜም እግሩና ቐርጭምጭምቱ ጸና።

[8] ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።

[9] ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት።

[10] እርሱም መልካም በምትባለው በመቅደስ ደጃፍ ተቀምጦ ምጿት ይለምን የነበረው እንደ ሆነ ዐወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መገረምና መደነቅ ሞላባቸው።

[11] ጴጥሮስና ዮሐንስም ይዘውት ወደ መቅደስ ሲገቡ ሕዝቡ ሁሉ ደንግጠው ወደ ሰሎሞን መመላለሻ ወደ እነርሱ ሮጡ።

[12] ጴጥሮስም ሕዝቡን ባያቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው ፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ለምን ታደንቃላችሁ? እኛንስ በኀይላችንና በጽድቃችን ይህን ሰው በእግሩ እንዲሄድ እንዳደረግነው አስመስላችሁ ለምን ታዩናላችሁ?

[13] የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ፥ የአባቶቻችንም አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትን፥ እርሱም ሊተወው ወዶ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ልጁን ኢየሱስን ገለጠው።

[14] እናንተ ግን ቅዱሱንና ጻድቁን ካዳችሁት፤ ነፍሰ ገዳዩን ሰውም እንዲያድንላችሁ ለመናችሁ።

[15] የሕይወትን ባለቤት ግን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ምስክሮቹ ነን።

[16] ስሙን በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፤ እርሱንም በማመን በፊታችሁ ይህን ሕይወት ሰጠው።

[17] “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ፥ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ።

[18] እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረ እንዲሁ ፈጸመ።

[19] እንግዲህ ኀጢአታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ ንስሓ ግቡ፥ ተመለሱም።

[20] ከእግዚአብሔር ዘንድም የይቅርታ ዘመን ይመጣል። አስቀድሞ የመረጠውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ይልክላችኋል።

[21] እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እስከ ተናገረው የመደራጀት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባል።

[22] ሙሴም አባቶቻችንን እንዲህ ብሎአቸዋል ፥ እግዚአብሔር አምላካችን ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙት።

[23] ያን ነቢይ የማትሰማው ነፍስም ሁሉ ከወገኖችዋ ተለይታ ትጥፋ።

[24] ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀኖች ተናግረዋል፤ አስተምረዋልም።

[25] እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በሠራው ሥርዐትም የተወለዳችሁ ናችሁ፤ ለአብርሃም ፥ ‘በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ’ ብሎታልና።

[26] እግዚአብሔርም አስቀድሞ ልጁን አስነሣላችሁ፤ ሁላችሁም ከክፋታችሁ እንድትመለሱ ይባርካችሁ ዘንድ ላከው።”

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters