Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:04

[1] ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራን ከተማም ደረሰ፤ እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ አባቱ ግን አረማዊ ነበረ።

[2] በደርቤንና በልስጥራን በኢቆንዮንም ያሉ ወንድሞች ሁሉ ይመሰክሩለት ነበር።

[3] ጳውሎስም ከእርሱ ጋር ይዞት ሊሄድ ወደደ፤ በዚያም ሀገር ስለ አሉት አይሁድ ወስዶ ገረዘው፤ አባቱ አረማዊ እንደ ነበረ ሁሉም ያውቁ ነበርና።

[4] በየከተማውም ሲሔዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን ሥርዐት አስተማሩአቸው።

[5] አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ፤ ዕለት ዕለትም ቐጥራቸው ይበዛ ነበር።

[6] ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በእስያ እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለከለከላቸው ወደ ፍርግያና ወደ ገላትያ አውራጃ ሄዱ፤

[7] ሚስያ በደረሱ ጊዜም ወደ ቢታንያ ሊሄዱ ወደዱ፤ የጌታችን ኢየሱስ መንፈስ ግን አልፈቀደላቸውም።

[8] ከሚስያም ዐልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ።

[9] ለጳውሎስም በሌሊት አንድ መቄዶናዊ ሰው ቁሞ ፥ “ወደ እኛ ወደ መቄዶንያ ዕለፍና ርዳን ” እያለ ሲማልደው በራእይ ተገለጸለት።

[10] ራእዩንም ባየ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ መቄዶንያ ልንሄድ ወደድን፤ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር የሚጠራን መስሎናልና።

[11] ከጢሮአዳም ወጥተን ወደ ሰሞትራቄ ገባን፤ በማግሥቱም ናጶሊ ወደምትባለው ሀገር በመርከብ መጣን።

[12] ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ሄድን፤ ይህችውም የመቄዶንያ ዋና ከተማና የሮም ቅኝ ግዛት ነበረች፤ በዚያችም ሀገር ጥቂት ቀን ሰነበትን።

[13] በሰንበት ቀንም ከከተማዉ በር ወደ ባሕሩ ዳር ወጣን፤ በዚያ የጸሎት ቤት ያለ መስሎን ነበርና፤ በዚያም ተቀምጠን፥ በዚያ ለተሰበሰቡ ሴቶች እናስተምር ጀመርን።

[14] በመካከላቸውም ቀይ ሐር የምትሸጥ ከትያጥሮን ሀገር የመጣች እግዚአብሔርን የምትፈራ አንዲት ሴት ነበረች፤ እግዚአብሔርም ልቡናዋን ከፍቶላት ነበርና ጳውሎስ የሚያስተምረውን ታዳምጥ ነበር፤ ስምዋም ልድያ ይባል ነበር።

[15] እርስዋም ከቤተ ሰቦችዋ ጋር ተጠመቀች፤ “ለእግዚአብሔር አማኝ ካደረጋችሁኝስ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እደሩ ” ብላ ማለደችን፤ የግድም አለችን።

[16] ለጸሎት ስንሄድም የምዋርተኛነት መንፈስ ያደረባት አንዲት ልጅ አገኘችን፤ በጥንቈላም የምታገኘውን ብዙ እጅ መንሻ ለጌቶችዋ ታገባ ነበር።

[17] ከዚህም በኋላ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች ፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፤ የሕይወትንም መንገድ ያስተምሩአችኋል” እያለች ትጮኽ ነበር።

[18] ብዙ ቀንም እንዲሁ ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስንም አሳዘነችው፤ መለስ ብሎም ፥ “መንፈስ ርኩስ፥ ከእርስዋ እንድትወጣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ ” አለው፤ ወዲያውኑም ተዋት።

[19] ጌቶችዋም የምታገባላቸው የጥቅማቸው ተስፋ እንደ ቀረ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው በገበያ እየጐተቱ ወደ ገዢዎች ወሰዱአቸው።

[20] ወደ ገዢዎችም አቅርበው ፥ “እነዚህ ሰዎች ከተማችንን ያሸብሩብናል፤ እነርሱም አይሁድ ናቸው።

[21] እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆንም ልናደርገው የማይገባንን ሕግ ይናገራሉ ” አሉ።

[22] ሕዝቡም ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፍፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ።

[23] በብዙም ደብድበው አሰሩአቸው፤ የወህኒ ቤቱን ዘበኛም አጽንቶ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።

[24] እርሱም ትእዛዙን ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ቤት አስገባቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው።

[25] በመንፈቀ ሌሊትም ጳውሎስና ሲላስ ጸለዩ፤ እግዚአብሔርንም በዜማ አመሰገኑት፤ እስረኟቹም ይሰሙአቸው ነበር።

[26] ድንገትም ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ፤ የወህኒ ቤቱ መሠረትም ተናወጠ፤ በሮችም ሁሉ ያንጊዜ ተከፈቱ፤ የሁሉም እግር ብረቶቻቸው እየወለቁ ወደቁ።

[27] የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ በሮች ሁሉ ተከፍተው አየ፤ ሰይፉንም መዝዞ ራሱን ሊገድል ወደደ፤ እስረኟቹ ያመለጡት መስሎት ነበርና።

[28] ጳውሎስም ፥ “በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ሁላችንም ከዚህ አለን ” ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ።

[29] መብራት አምጥቶም እየተንቀጠቀጠ ወደ ውስጥ ሄደና ለጳውሎስና ለሲላስ ወድቆ ሰገደ።

[30] ወደ ውጭም አውጥቶ “ጌቶቼ፥ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው።

[31] እነርሱም ፥ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰብህም ሁሉ ትድናላችሁ ” አሉት።

[32] የእግዚአብሔርንም ቃል ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሁሉ ነገሩአቸው።

[33] ወዲያውኑም በሌሊት ወስዶ ቐስላቸውን አጠበላቸው፤ እርሱም በዚያው ጊዜ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቀ።

[34] ወደ ቤቱም አግብቶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በጌታችን ስለ አመነም እርሱ ከቤተ ሰቡ ጋር ደስ አለው።

[35] በነጋ ጊዜም፥ ገዢዎቹ ፥ “እነዚያን ሰዎች ፈትታችሁ ልቀቌቸው ” ብለው ብላቴኖቻቸውን ላኩ።

[36] የወህኒ ቤቱ ጠባቂም በሰማ ጊዜ ሄዶ ገዢዎቹ “ይፈቱ” ብለው እንደ ላኩ ይህን ነገር ለጳውሎስና ለሲላስ ነገራቸው፤ “አሁንም ውጡና በሰላም ሂዱ ” አላቸው።

[37] ጳውሎስ ግን ፥ “እኛ የሮም ሰዎች ስንሆን፥ ያለ ፍርድ በአደባባይ ገረፉን፤ አሰሩንም፤ አሁንም በስውር ሊያወጡን ይሻሉ፤ አይሆንም፥ ራሳቸው መጥተው ያውጡን ” አላቸው።

[38] ብላቴኖቻቸውም ሄደው ይህንን ነገር ለገዢዎቹ ነገሩአቸው፤ የሮም ሰዎች መሆናቸውንም ሰምተው ደነገጡ።

[39] መጥተውም ከከተማቸው እንዲወጡ ማለዱአቸው።

[40] ከወኅኒ ቤቱም ከወጡ በኋላ ወደ ልድያ ቤት ገብተው ወንድሞችን አገኙ፤ አጽናንተዋቸውም ሔዱ።

የሐዋርያት ሥራ። — Chapters