Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:10

[1] ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳየው ፈጥኖ ይሆን ዘንድ ያለውንና ከዚያም በኋላ የሚሆነውን ለአገልጋዮቹ ይገልጽላቸው ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠው፥ በመልአኩም አማካይነት ወደ ባለሙአሉ ወደ ዮሐንስ የላከው ራእይ ይህ ነው።

[2] እርሱም ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት በአየው ሁሉ መሰከረ።

[3] ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የዚህንም መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚሰሙትና በውስጡም የተጻፈውን የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው።

[4] ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የጻፈው ፥ ካለውና ከነበረው፥ ከሚመጣውም በኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ፊት ካሉ ከሰባቱ መናፍስት፥

[5] ከታመነውም ምስክር፥ ከሙታን በኵuር፥ የምድር ነገሥታት ገዥም ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን፥ ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥

[6] ነገሥታትም፥ ለአባቱም ለእግዚአብሔር ካህናት ለአደረገን ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብርና ኀይል ይሁን፤ አሜን።

[7] እነሆ፥ በሰማይ ደመና ይመጣል፤ ዐይን ሁላ ታየዋለች፥ እነዚያም የወጉት ይመለከቱታል፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስለ እርሱ ያለቅሳሉ፤ አዎን፥ አሜን።

[8] የነበረውና ያለው፥ የመጣውና የሚመጣውም፥ ሁሉንም የሚገዛ እግዚአብሔር አምላክ ” አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ” ይላል።

[9] እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ፥ ከእናንተ ጋርም አብሬ መከራውንና መንግሥቱን፥ የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክርነት ፍጥሞ በምትባል ደሴት ሳለሁ፥

[10] በእሑድ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወደ እኔ መጣ፤ ከወደ ኋላዬም እንደ መለከት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅን ሰማሁ።

[11] “እንግዲህ የምታየውንና የምትሰማውን በመጽሐፍ ጽፈህ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ለኤፌሶንና ለሰሚርኔስ፥ ለጴርጋሞንና ለትያጥሮን፥ ለሰርዴስና ለፊልድልፍያ፥ ለሎዶቅያም ላክ ” አለኝ።

[12] ከእኔም ጋር የሚነጋገረውን ያንን ድምፅ አይ ዘንድ ዘወር አልሁ፤ ዘወር ባልሁ ጊዜም እነሆ፥ ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ።

[13] በሰባቱ መቅረዞች መካከልም የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ የሚደርስ ልብስ የለበሰ፥ ወገቡንም በወርቅ ዝናር የታጠቀ ነበር።

[14] ራሱና የራስ ጠጕuሩም እንደ ነጭ የበግ ጠጕuር፥ እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ።

[15] እግሮቹም በእሳት የነጠረና የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ ነበረ።

[16] በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩ፤ ከአንደበቱም ሁለት አፍ ያለው የተሳለ ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኀይል እንደሚያበራ ፀሓይ ነበረ።

[17] በአየሁትም ጊዜ፥ ከእግሩ ሥር ወደቅሁ፤ እንደ ሞተ ሰውም ሆንሁ፤ በቀኝ እጁም ያዘኝ፤ እንዲህም አለኝ ፥ “አትፍራ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፤

[18] ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእኔ ዘንድ አለ።

[19] እንግዲህ ያየኸውን፥ አሁንም ያለውን፥ ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።

[20] በቀኜ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ትርጓሜያቸው ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አለቆች ናቸው፤ እነዚያ ሰባቱ መቅረዞችም ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters