Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:30

[1] ከዚህም በኋላ ፥ “ሃሌ ሉያ ማዳንና ክብር፥ ኀይልም ለአምላካችን ነው፤

[2] በዝሙቷ ምድርን ያጠፋችውን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ ፍርዱ እውነትና ጽድቅ ነው ” የሚል እንደ ብዙ ሰው ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅን ከሰማይ ሰማሁ።

[3] ዳግመኛም “ሃሌ ሉያ፥ ጢስም ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይወጣል ” አሉ።

[4] እነዚያ ሀያ አራቱ አለቆችና አርባዕቱ እንስሳም በቅዱስ ዙፋን ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር ፥ “አሜን፥ ሃሌ ሉያ ” እያሉ ሰገዱ።

[5] ከሰማይም ከዙፋኑ ፥ “ባሪያዎቹ ሁሉ፥ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፥ አምላካችንን አመስግኑ ” የሚል ድምፅ ወጣ።

[6] ከዚህም በኋላ እንደ ብዙ ሰው ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውኃም ድምፅ፥ እንደ ነጐድጓድም ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ፤ እንዲህ ሲል ፥ “ሃሌ ሉያ ሁሉን የሚገዛ አምላካችን እግዚአብሔር ነግሦአልና።

[7] የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፥ ሙሽራይቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ፤ ለእርሱም ክብርን እናቅርብ።

[8] ንጹሕ የብርሃን ልብስም እንድትለብስ ተሰጣት፤ ያም የብርሃን ልብስ የቅዱሳን ጽድቅ ነው።”

[9] እርሱም ፥ “ወደ በጉ ሰርግ በዓል የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ” ብለህ ጻፍ አለኝ፤ ደግሞም ፥ “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው ” አለኝ።

[10] ከእግሩ በታችም ወድቄ ሰገድሁለት፤ እንዲህም አለኝ ፥ “እኔም እንደ አንተ፥ ከአንተም ጋር፥ የኢየሱስን ምስክርነት ከሚጠብቁት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝና እንዳትሰግድልኝ ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ስገድ፥ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና።”

[11] ከዚህም በኋላ ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፤ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፤ በጽድቅም ይፈርዳል፤ ይዋጋልም።

[12] ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው።

[13] በደም የታለለ ልብስም ለብሶአል፤ ስሙንም “ቃለ እግዚአብሔር ” አሉት።

[14] የሰማይ ጭፍሮችም ንጹሕ የብርሃን ልብስ ለብሰው፥ በአምባላዮች ፈረሶችም ተቀምጠው፥ ይከተሉት ነበር።

[15] አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ፥ ከአፉ የተሳለ ሰይፍ ይወጣል፤ እርሱም በብረት ዘንግ ይጠብቃቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ፥ የእግዚአብሔርን የቐጣውን መቅሠፍት ወይን መጭመቂያ ይረግጣል።

[16] በልብሱ ላይና በጎኑ ላይ፥ “የነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ ” የሚል ስም ተጽፎበታል።

[17] ከዚህም በኋላ አንድ መልአክ በፀሓይ ላይ ቆሞ አየሁ፤ በታላቅ ቃልም እየጮኸ በሰማይ መካከል ለሚበርሩ አዕዋፍ ሁሉ እንዲህ አለ ፥ “ኑ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር በዓል ተሰብሰቡ።

[18] የነገሥታቱን ሥጋ፥ የሻለቆቹንም ሥጋ፥ የኀያላኑንም ሥጋ፥ የፈረሶችንና የፈረሰኟችንም ሥጋ፥ የጌቶችንና የባሪያዎችንም ሥጋ፥ የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሥጋ ትበሉ ዘንድ ተሰብሰቡ።”

[19] ከዚህ በኋላ፥ ያ ቀድሞ ያየሁት አውሬ ወጣ፤ የምድር ነገሥታትም፥ ያን በአምባላይ ፈረስ የተቀመጠውን ከነሠራዊቱ ይወጉት ዘንድ ከነሠራዊታቸው ከእርሱ ጋር ተሰብስበው አየሁ።

[20] ከዚህም በኋላ አውሬው ተያዘ፤ በእርሱም ፊት ተአምራትን አደረገ፤ የአውሬውንም ምልክት የተቀበሉትን፥ ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ።

[21] የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ የሰማይ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters