Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:36

[1] ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኩል ሰዓት ያህል በሰማይ ጸጥታ ሆነ።

[2] በእግዚአብሔርም ፊት የቆሙ ሰባት መላእክትን አየሁ፤ ሰባት ቀንደ መለከቶችም ተሰጡአቸው።

[3] ሌላ መልአክም መጣ፤ በመሠዊያው ፊትም ቆመ፤ የወርቅ ጥናም ይዞ ነበር፤ በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቁ መሠዊያም ላይ፥ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲያሳርገው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።

[4] የዕጣኑ ጢስም ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐረገ።

[5] መልአኩም ጥናውን ይዞ ከመሠዊያው እሳት ሞላበት፤ ወደ ምድርም ጣለው፤ ወደ ምድርም በጣለው ጊዜ ነጐድጓድና ብልጭልጭታ፥ መብረቅም፥ መናወጥም ሆነ።

[6] ሰባቱንም ቀንደ መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ቀንደ መለከቶችን ሊነፉ ተዘጋጁ።

[7] አንደኛውም መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ ከደም ጋር የተቀላቀለ በረድና እሳት ሆነ፤ በምድር ላይም ወረደ፤ የምድርም ሲሶዋ ተቃጠለ፤ የዛፎችም፥ የለመለመውም ሣር ሁሉ ሲሶው ተቃጠለ።

[8] ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ ተራራ የሚያህል ታላቅ እሳት እየነደደ ወደ ባሕር ወረደ፤ የባሕርም ሲሶዋ ደም ሆነ።

[9] በባሕርም ውስጥ ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሲሶአቸው ጠፋ።

[10] ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ፥ እንደ ችቦ የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወረደ፤ በወንዞችና በውኃ ምንጮች ሲሶ ላይም ወደቀ።

[11] የዚያም ኮከብ ስሙ እሬቶ ነው፤ የውኃዎችም ሲሶአቸው ሬት ሆነ፤ ከውኃዎችም ምረት የተነሣ የሞተው ሰው ብዙ ነው።

[12] አራተኛውም መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ የፀሓይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ፥ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፤ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንና የሌሊትም ሲሶአቸው እንዳያበራ ጨለመ።

[13] አየሁም፥ አንድ ንስር በሰማይና በምድር መካከል፥ እየበረረ በታላቅ ድምፅም ፥ “ይነፉ ዘንድ ካላቸው ከቀሩት ከሦስቱ መላእክት መለከት ድምፅ የተነሣ በምድር ለሚኖሩ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው” ሲል ሰማሁ።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters