[1] ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የተጐናጸፈች፥ ጨረቃንም ከእግሯ በታች የተጫማች፥ በራስዋ ላይም ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉበት አክሊል የተቀዳጀች አንዲት ሴት ነበረች።
[2] ሴቲቱም ፀንሳ ነበረች፥ ለመውለድም ምጥ ተይዛ ትጮህ ነበር።
[3] ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፥ ታላቅ ቀይ ዘንዶ፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩት።
[4] በጅራቱም የሰማይ ከዋክብትን ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር አወረዳቸው፤ ዘንዶውም በወለደች ጊዜ ልጅዋን ሊበላ በዚያች ሴት ፊት አንጻር ቆመ።
[5] አሕዛብንም ሁሉ በብረት ዘንግ የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር፥ ወደ ዙፋኑም ተወሰደ።
[6] ሴቲቱም በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በረሃ ሸሸች።
[7] በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፤ ዘንዶውም ከነሠራዊቱ ተዋጋቸው።
[8] አልቻላቸውምም፤ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘላቸውም።
[9] ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።
[10] በሰማይም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ ፥ “የአምላካችን ማዳንና ኀይል፥ መንግሥትም፥ የመሢሑም ሥልጣን ሆነች፤ አባቶቻችንን በእግዚአብሔር ፊት በቀንና በሌሊት ሲያጣላቸው የነበረ ከሳሽ ወድቆአልና።
[11] እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ፥ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፤ ሰውነታቸውን እስከ ሞት ድረስ አልወደዱምና።
[12] ስለዚህ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ነገር ግን ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው! ሰይጣን ጥቂት ዘመን እንዳለው ዐውቆ፥ ከክፉ መርዙ ጋር ወደ እናንተ ወርዶአልና።”
[13] ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ወደቀ ባየ ጊዜ፥ ወንድ ልጅ የወለደችውን ያቺን ሴት አሳደዳት።
[14] ለሴቲቱም ከዘንዶው ፊት ርቃ፥ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኩሌታ ወደምትጠበቅበት ቦታ ወደ በረሃ እንድትበርር ሁለት የታላቁ ንስር ክንፎች ተሰጧት። ዘንዶውም በርሮ ተከተላት።
[15] ዘንዶውም ጎርፉ ይወስዳት ዘንድ፥ ከአፉ እንደ ታላቅ ወንዝ ያለ ብዙ ውኃ በዚያች ሴት በስተኋላ አፈሰሰ።
[16] ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፤ ምድርም አፍዋን ከፍታ፥ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ውኃ መጠጠችው። ነገር ግን ለሴቲቱ ክንፍ እንደ ተሰጣት አላወቀም።
[17] ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርም ያላቸውን የቀሩትን ልጆችዋን ሊወጋቸው ሄደ።
[18] ዘንዶውም በባሕሩ አሸዋ ላይ ቆመ።