[1] ሰባቱን ጿዎች ከያዙት ከእነዚያ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ ፥ “ና፥ በብዙም ውኃ ላይ የምትኖረውን የዚያችን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤” አለኝ።
[2] “እርስዋም የምድር ነገሥታት ያመነዘሩባት፥ በምድር ላይ የሚኖሩም ከዝሙቷ ወይን ጠጅ የሰከሩባት ናት ” ብሎ ተናገረኝ።
[3] ከዚህም በኋላ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደኝ፤ የስድብ ስሞችም በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ።
[4] ያቺ ሴትም የነጭ ሐርና የቀይ ሐር፥ የከበረ ዕንቐና አልማዞችም ያሉበት የወርቅ ልብስ ለብሳለች፤ በእጅዋም ርኵuሰትንና የዝሙትን በደል የተሞላውን የወርቅ ጿ ይዛለች።
[5] በግንባርዋም “ታላቂቱ ባቢሎን የምድር ርኵuሰት ምንጭና የአመንዝሮች እናት ” የሚል የምሥጢር ስም ተጽፎባታል።
[6] ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት፤ በአየኋት ጊዜም አደነቅኋት፤ እጅግም ተገረምሁ።
[7] ያ መልአክም እንዲህ አለኝ ፥ “የምትደነቀው ስለምን ነው? የዚያችን ሴት ምሥጢርና የሚሸከማትን ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምሥጢር እኔ እነግርሃለሁ።
[8] ያም ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፤ ወደ ጥፋትም ይሔዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ፥ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደ ነበር፥ አሁንም እንደሌለ፥ ወደፊት ግን ይመጣ ዘንድ እንዳለው ሲያዩ ያደንቃሉ።
[9] ልብና ዕውቀት ያለውም ይህን ያውቀዋል፤ የዚህም የአየኸው አውሬ ሰባቱ ራሶቹ ያቺ ሴት የምትኖርባቸው ሰባቱ ተራሮች ናቸው።
[10] ሰባቱ ተራሮችም ሰባቱ ነገሥታት ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ ብቻ አለ፤ አንዱ ግን ገና አልመጣም፤ ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቈይ ይገባዋል።
[11] ያ የነበረውና የሌለውም አውሬ ስምንተኛው ነው፤ ከእነዚህ ከሰባቱ ጋርም እርሱ ወደ ጥፋት ይሔዳል።
[12] እነዚህ ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች መንግሥታቸው ገና ያልጸናች ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከዚያ አውሬ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይይዛሉ።
[13] ምክራቸው አንድ ነው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለዚያ አውሬ ይሰጣሉ።
[14] ከበጉም ጋር ይዋጋሉ፤ በጉም ያሸንፋቸዋል፤ የጌቶች ጌታ ነውና፥ የንጉሦችም ንጉሥ ነውና፤ ከእርሱም ጋር ያሉት ስመ ጥሩዎች ምርጦችና ታማኟች ናቸው።
[15] “እነዚያ ያየሃቸው ውኃዎችም፥ ያቺ ጋለሞታ ሴት የምትኖርባቸው አሕዛብና ሕዝብ፥ ነገዶችና የልዩ ልዩ ወገን ሰዎች ናቸው።
[16] እነዚያ ዐሥሩ ቀንዶችና ያየኸው ያ አውሬ፥ እነርሱ ያቺን ጋለሞታ ይሸምቁባታል፤ ያጠፉአታልም፤ ያራቁቱአታልም፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ እርስዋን ግን በእሳት ያቃጥሉአታል።
[17] እግዚአብሔርም አሳቡን እንዲያደርጉ በአንድ ምክርም እንዲተባበሩ፥ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ እግዚአብሔር በልባቸው አሳድሮባቸዋልና።
[18] ያየሃት ያቺ ሴትም በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”