[1] ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክትን አየሁ፥ እነርሱም ነፋስ በምድር ላይ፥ ወይም በባሕር ላይ፥ ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ፥ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አገዱ።
[2] የሕያው እግዚአብሔርን ማኅተም የያዘ ሌላ መልአክም ከምሥራቅ ሲወጣ አየሁ፤ የብስንና ባሕርን ሊጎዱ ሥልጣን ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክትም በታላቅ ድምፅ እየጮኸ፥
[3] “የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትምባቸው ድረስ፥ ምድርንም ቢሆን፥ ወይም ባሕርን፥ ወይም ዛፎችን በአንድ ጊዜ አታጥፉ ” አላቸው።
[4] የታተሙትንም ቐጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።
[5] ከነገደ ይሁዳ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ሮቤል ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ጋድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
[6] ከነገደ አሴር ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ንፍታሌም ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ምናሴ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
[7] ከነገደ ስምዖን ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ሌዊ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ይሳኮር ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
[8] ከነገደ ዛብሎን ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ዮሴፍ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከነገደ ብንያም ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፤ እንግዲህ የታተሙ እነዚህ ናቸው።
[9] ከዚህም በኋላ ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ብዙ ሰዎችን አየሁ፤ ከሕዝብና፥ ከአሕዛብ፥ ከነገድና ከልዩ ልዩ ወገን፥ በዙፋንና በበጉ ፊት ቆመዋል፤ ነጭ ልብስም ለብሰዋል፥ በእጃቸውም ዘንባባ ይዘዋል።
[10] በታላቅ ቃልም ፥ “በዙፋኑ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ይገባል ” እያሉ ይጮኻሉ።
[11] መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በአለቆቹ፥ በአራቱም እንስሶች ዙሪያ ቁመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግንባራቸው ሰገዱ።
[12] ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ እንዲህ አሉ ፥ “አሜን፥ ምስጋናና ጥበብ፥ በረከትና ውዳሴ፥ ኀይልና ብርታትም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለአምላካችን ይሁን አሜን።”
[13] ከአለቆችም አንዱ ፥ “እነዚህ ነጫጭ ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከየትስ መጡ?” አለኝ።
[14] እኔም ፥ “አቤቱ፥ አንተ ታውቃለህ” አልሁት፤ እርሱም ፥ “እሊህ ከጽኑ መከራ የወጡ፥ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ያነጹ ናቸው ” አለኝ።
[15] ስለዚህም ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ቀረቡ፤ በመቅደሱ ውስጥም ቀንና ሌሊት ያመሰግኑታል፤ ያም በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ አድሮባቸው ይኖራል።
[16] ዳግመኛም አይራቡም፤ አይጠሙም፤ የፀሓይ ሐሩርም አያገኛቸውም።
[17] በዙፋኑ ፊት ያለው በጉ ይጠብቃቸዋልና፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።