[1] ከዚህም በኋላ ሌላ ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበር፤ ፊቱም እንደ ፀሓይ ብሩህ ነበር፤ እግሮቹም እንደ እሳት አዕማድ ነበሩ።
[2] በእጁም የተገለጠች ታናሽ መጽሐፍ ይዞአል፤ በቀኝ እግሩ በባሕር ላይ፥ በግራ እግሩም በምድር ላይ ቆሞአል።
[3] እንደሚያገሣ አንበሳም በታላቅ ቃል ጮኸ፤ በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ ይጻፍ ዘንድ ስላለው ነገር በየቃላቸው ተናገሩ።
[4] ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትንም ቃል ሰማሁ፤ ልጽፈውም ወደድሁ፤ ከዚህም በኋላ “ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትን፥ በምሥጢር ጠብቀው፤ አትጻፈውም ” የሚል ቃል ከሰማይ መጣ።
[5] በባሕርና በምድር ላይ ቁሞ፥ ያየሁት መልአክም ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ።
[6] ሰማይንና በውስጡ ያለውን ሁሉ፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ሁሉ፥ ባሕርንና በውስጡ ያለውንም ሁሉ በፈጠረው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ ፥ “ወደ ፊት አይዘገይም።
[7] ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ይነፋ ዘንድ በአለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት የምሥራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል ” አለ።
[8] ያ ከሰማይ የሰማሁት ቃልም፥ ዳግመኛ ተናገረኝ፤ እንዲህም አለ ፥ “ሂድ ያቺን የተገለጠችውን፥ በባሕርና በምድር ላይ በቆመው በዚያ መልአክ እጅ ያለችውን መጽሐፍ ውሰድ።”
[9] ወደዚያ መልአክም ሄጄ ፥ “ያችን መጽሐፍ ስጠኝ ” አልሁት፤ እርሱም ፥ “ ውሰዳትና ብላት፤ ሆድህንም ትምረራት፤ በአፍህ ግን፥ እንደ መዓር የምትጣፍጥ ትሁንህ ” አለኝ።
[10] ያቺንም መጽሐፍ ከዚያ መልአክ እጅ ተቀብዬ በላኋት፤ በአፌም የምትጣፍጥ ሆነችኝ፤ በዋጥኋት ጊዜ ግን ሆዴን አመረረቻት።
[11] እንደ ገና ፥ “ለአሕዛብና ለሕዝብ፥ ለሀገሮችና ለብዙ ነገሥታትም ትንቢት ትናገር ዘንድ አለህ ” አለኝ።