Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:50

[1] ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወት ውኃ ወንዝንም አሳየኝ።

[2] በዐደባባይዋ መካከልም ይፈስሳል፤ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠል ለአሕዛብ ሕይወት ፈውስ ነበር።

[3] ከእንግዲህም ወዲህ ምንም መርገም አይኖርም፤ በውስጥዋም የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን ይሆናል፤ በሚያመልኩት በእግዚአብሔር አገልጋዮችም ላይ ቅWጣ አይሆንም።

[4] ፊቱንም ያያሉ፤ ስሙም በግንባራቸው ይሆናል።

[5] ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ የመብራት ብርሃን፥ ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ያበራላቸዋልና፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ።

[6] እርሱም እንዲህ አለኝ ፥ “ይህ ቃል የታመነና እውነተኛ ነው፤ የነቢያትም መናፍስት ጌታ ከእግዚአብሔር ፈጥኖ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ ይገልጥላቸው ዘንድ መልአኩን ላከ።

[7] እነሆ፥ ፈጥኜ እመጣለሁ፥ ይህ መጽሐፍ የተናገረውንም ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”

[8] ይህን ያየሁና የሰማሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ፤ ይህን በሰማሁና በአየሁ ጊዜም ያንጊዜ ይህን በአሳየኝ በዚያ መልአክ እግር ሥር ሰገድሁ።

[9] እርሱ ግን እንዲህ አለኝ ፥ “ለእኔ እንዳትሰግድ ተጠንቀቅ፥ እኔም ከአንተ ጋር፥ ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር፥ የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፥ አንተስ ለእግዚአብሔር ስገድ።

[10] የዚህንም መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤ ዘመኑ ቀርቦአልና፤

[11] እንግዲህ ግፍ የሚሠራው ወደፊት ግፍ ይሥራ፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።”

[12] “እነሆ፥ ፈጥኜ፥ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።

[13] አልፋና ዖሜጋ፥ ቀዳማዊና ድኃራዊ፤ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።”

[14] ወደ ሕይወት ዛፍም ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው፥ በደጆችዋም ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ፥ ልብሳቸውን የሚያነጹ ብፁዓን ናቸው።

[15] አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች ሀገር ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ እነዚህም ፥ አስማተኟች፥ ዘማውያን፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት የሚያመልኩ፥ የሐሰት ሥራንም ሁሉ የሚወዱ ሁሉ ናቸው።

[16] “እኔ ኢየሱስ ለእናንተ ለአብያተ ክርስቲያናት ይህን ይመሰክርላችሁ ዘንድ መልእክተኛዬን ላክሁ፤ እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የአጥቢያ ኮከብ እኔ ነኝ።”

[17] መንፈሱና ሙሽራይቱም “ና ” ይላሉ። የሚሰማም “ና ” ይበል። “የሚሰማም ና ይበል” የሚለውንም አይጨምርም። የተጠማ ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውኃ ያለዋጋ ይውሰድ።

[18] የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ ምስክሩ እኔ ነኝ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር፥ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን መቅሠፍት ይጨምርበታል።

[19] ማንም ከዚህ የትንቢት መጽሐፍ ቃል ቢያጐድል በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጐድልበታል።

[20] ይህን የሚመሰክር ፥ “አዎን፥ ፈጥኜ እመጣለሁ ” ይላል፤ አሜን፥ ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ ና።

[21] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ቅዱስ ዮሐንስ ያየው ራእይ በዚህ ተፈጸመ፥ ይህም በሕይወቱ ያየው ራእይ ነው። አሜን።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters