Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:51

[1] በትር የሚያህል የወርቅ ዘንግ ሰጠኝ፤ እንዲህም አለኝ ፥ “ተነሣና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን፥ የሚሰግዱበትንም ለካ።

[2] የውጭው አደባባይ ግን ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተው አትለካ፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።

[3] ሁለቱን ጻድቃኖቼንም ማቅ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ይናገሩ ዘንድ አዝዛቸዋለሁ።”

[4] እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።

[5] ከጠላቶቻቸውም ሊጎዳቸው የፈቀደ ቢኖር ከአፋቸው እሳት ወጥታ ጠላቶቻቸውን ታጠፋቸዋለች፤ የሚጠሉአቸውም ሁሉ እንዲሁ ይሞታሉ።

[6] እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ይዘጉት ዘንድ ሥልጣን አላቸው፤ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ሥልጣን አላቸው።

[7] ምስክርነታቸውንና ትንቢታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸዋልም፤ ይገድላቸዋልም።

[8] በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይቀመጣል፤ እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብፅ የተባለች ደግሞም ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።

[9] በድናቸውንም ሦስት ቀን ተኩል አሕዛብና ሕዝብ፥ ነገድና በልዩ ልዩ ሀገር የሚኖሩ ወገኖች ያዩታል። በድናቸውንም በመቃብር እንዲቀብሩት አይፈቅድም።

[10] እነዚህ ሁለቱ ነቢያት በምድር ላይ የሚኖሩትን አስጨንቀዋቸው ስለ ነበር በምድር ላይ የሚኖሩ በእነርሱ ደስ ይላቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም እጅ መንሻ ይሰጣጣሉ ።

[11] ከሦስት ቀን ተኩል በኋላም የሕይወት መንፈስ ከእግዚአብሔር ወጥታ አደረችባቸው፤ በእግራቸውም ቀጥ ብለው ቆሙ፤ በሚያዩአቸው ላይም ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው።

[12] ከሰማይም ታላቅ ድምፅ መጥቶ ፥ “ወደዚህ ውጡ ” አላቸው፤ ጠላቶቻቸውም እያዩአቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ።

[13] በዚያች ሰዓትም ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማዪቱም ዐሥረኛዋ እጅ ወደቀ፤ በዚያም መናወጥ ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ የቀሩትም ደነገጡ፤ የሰማይ አምላክንም አከበሩት፤

[14] በዚህም ሁለተኛዪቱ መከራ አለፈች፤ ሦስተኛዪቱም መከራ ፈጥና ትመጣለች።

[15] ሰባተኛው መልአክም መለከት በነፋ ጊዜ “የዓለም መንግሥት ለእግዚአብሔርና ለመሢሑ ሆነች፤ ለዘለዓለሙም ይነግሣል ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከሰማይ መጣ።

[16] በእግዚአብሔር ፊት በየወንበራቸው የተቀመጡት እነዚያ ሃያ አራት አለቆችም በግንባራቸው ወድቀው ለግዚአብሔር ሰገዱ።

[17] እንዲህም አሉ ፥ “አቤቱ፥ ሁሉን የምትገዛ፥ የነበርህና፥ የምትኖር እግዚአብሔር ሆይ፥ እናመሰግንሃለን፤ ታላቁን ኀይልህን አንሥተሃልና፥ ነግሠሃልምና።

[18] አሕዛብ ግን ተበሳጩ፤ ቅWጣህ ደርሶባቸዋልና፤ ሙታን ይፈረድባቸው ዘንድ ለባሮችህ ለነቢያትና ለቅዱሳን፥ ስምህንም ለሚፈሩ ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጣቸው ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉአትን ትቀጣቸው ዘንድ ዘመናቸው ደርሶአል።”

[19] ከዚህም በኋላ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፤ የእግዚአብሔር የሕጉ ታቦትም በመቅደሱ ታየች፤ የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ፥ የምድር መናወጥና ታላቅ በረድም ሆነ።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters