Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:26

[1] “ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍ ፥ ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘው፥ በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል ፥

[2] “ሥራህንና ድካምህን፥ ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ሳይሆኑም ሐዋርያት ነን የሚሉትን ክፉዎቹን መታገሥ እንዳልቻልህ፥ ሐሰተኟችም ሆነው እንደ አገኘሃቸው አውቃለሁ።

[3] ስለ ስሜም ብለህ ታገሥህ፥ ቻልህ፥ አልደከምህምም።

[4] ነገር ግን አንተን የምነቅፍበት ነገር አለኝ፤ የቀድሞ ፍቅርህን ትተሃልና።

[5] ከወዴት እንደ ወደቅህ ዐስብ፤ እንግዲህ ንስሓ ግባ፥ ያለዚያ ንስሓ ባትገባ የቀድሞ ሥራህንም ባትሠራ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፤ መቅረዝህንም ከቦታዋ አነሣታለሁ።

[6] ነገር ግን ይህ አለህ፥ እኔ እንደምጠላው የኒቆላውያንን ሥራ ትጠላለህና።

[7] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው፥ በአምላክ ገነት ውስጥ ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።

[8] “ለሰሚርኔስ ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍለት ፥ ፊተኛውና መጨረሻው፥ ሞቶም የተነሣው እንዲህ ይላል።

[9] መከራህንና መቸገርህን አውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ ባለጠጋ ነህ፤ የሰይጣን ማኅበር ናቸው እንጂ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉትን ስድባቸውን አውቃለሁ፤

[10] ትቀበለውም ዘንድ ስላለህ መከራ፥ ምንም አትፍራ፤ እነሆ እንድትፈተኑ ሰይጣን ከእናንተ አንዳንዶችን ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ያደርጋል፤ ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ፤ እስከ ሞት ድረስም የታመንህ ሁን፤ የሕይወት አክሊልንም እሰጥሃለሁ።

[11] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ፤ ድል የነሣ ሁለተኛውን ሞት አይሞትም።

[12] “ለጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍ ፥ ሁለት አፍ የሆነ፥ የተሳለ ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል ፥

[13] የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፤ ሰይጣን በሚኖርበት ቦታ የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በእናንተ ዘንድ በተገደለበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም።

[14] ነገር ግን አንተን የምነቅፍበት ጥቂት ነገር አለ፤ የባላቅ መምህር የበለዓምን ትምህርት አጽንተው የያዙ፥ ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሰስኑ፥ በእስራኤል ልጆች ፊት ዕንቅፋት የሚያኖሩ በዚያ ካንተ ጋር አሉና።

[15] እንዲሁም የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚከተሉ ባንተ ዘንድ አሉ።

[16] እንግዲህ ንስሓ ግባ፤ ያለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፤ ከአፌ በሚወጣም ሰይፍ እወጋቸዋለሁ።

[17] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ስውር መናን እሰጠዋለሁ፤ የብርሃን መጽሐፍንም እሰጠዋለሁ፤ በዚያ መጽሐፍ ውስጥም ከተቀበለው በቀር ማንም የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎበታል።

[18] “ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍለት ፥ ዐይኖቹ የእሳት ነበልባል የሚመስሉ፥ እግሮቹም በእሳት የነጠረና የጋለ ናስ የሚመስሉ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል።

[19] ሥራህንና ፍቅርህን፥ እምነትህንም፥ አገልግሎትህንም፥ ትዕግሥትህንም የኋለኛዪቱ ሥራህም ከፊተኛይቱ ይልቅ እንደምትበዛ አውቃለሁ።

[20] ነገር ግን አንተን የምነቅፍበት ነገር አለኝ፤ ሳትሆን ራስዋን ነቢይት ነኝ የምትለውን፥ አገልጋዮቼንም ለጣዖት የተሠዋውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ዝም ብለሃታልና።

[21] ንስሓ እንድትገባም ጊዜ ሰጠኋት፤ ነገር ግን፥ ከዝሙቷ ንስሓ መግባትን እንቢ አለች።

[22] እነሆ፥ ወደ ቀደመ መኝታዋ እመልሳታለሁ፤ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራቸው ንስሓ ባይገቡ ወደ ጽኑዕ ሥቃይ አገባቸዋለሁ።

[23] ልጆችዋንም በሞት እገድላለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ልብንና ኵuላሊትን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ከእናንተም ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ።

[24] በትያጥሮን ለቀራችሁት፥ ይህም ትምህርት ለሌላችሁ፥ የሰይጣንንም ሽንገላ እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁአት ለእናንተ እንዲህ እላለሁ ፥ ሌላ ሸክም አላሸክማችሁም።

[25] ነገር ግን እስከምመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ።

[26] ድል ለነሣውና ሥራዬን እስከ መጨረሻ ለጠበቀው በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ።

[27] በብረት በትርም ይጠብቃቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቅጣቸዋል።

[28] እኔ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ የአጥቢያ ኮከብን እሰጠዋለሁ።

[29] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters