Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:58

[1] ከዚህ በኋላም ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ የጥልቁን መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለትም በእጁ ይዞ ነበር።

[2] የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን፥ እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አሰረው።

[3] ወደ ጥልቁም ጣለው፤ አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት፥ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማሕተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ አለው።

[4] ከዚህም በኋላ ዙፋኖች ተዘርግተው፥ የሰው ልጅም በላያቸው ተቀምጦ አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃልም ለተገደሉት ነፍሳት ቅን ፍርድን ፈረደላቸው፤ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን፥ በግምባራቸውና በእጃቸው ላይ ምልክቱን ያልጻፉትንም አየሁ፥ እነርሱም ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ኖረው ይነግሣሉ።

[5] ሌሎች ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ አይነሡም፤ ይህችም የመጀመሪያዪቱ ትንሣኤ ናት።

[6] አስቀድማ በምትመጣው ትንሣኤም ዕድል ያገኘ ሰው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ በእነርሱ ላይ ሁለተኛው ሞት ሥልጣን የለውም፤ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉና፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።

[7] ሺህም ዓመት በሚፈጸም ጊዜ፥ ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል።

[8] በአራቱም የምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ ያስት ዘንድ፥ ጎግንና ማጎግንም ለሰልፍ ይሰበስባቸው ዘንድ ይወጣል፤ ቐጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ ነው።

[9] ወደ ምድርም ስፋት ወጡ፤ የቅዱሳንን ሰፈርና ቅድስቲቱንም ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው።

[10] ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም በመዐልትና በሌሊት ይሠቃያሉ።

[11] ከዚህም በኋላ ታላቅና ነጭ ዙፋንን፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ሰማይና ምድርም ከፊቱ ሸሹ፤ ቦታም አልተገኘላቸውም።

[12] ከዚህም በኋላ ታናናሾችና ታላላቆች ሙታንን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ሁሉ ተገለጡ፤ ሌላም መጽሐፍ ተገለጠ፤ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት እንደ ተጻፈ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድ ተሰጣቸው።

[13] ባሕርም በውስጥዋ ያሉትን ሙታን ሁሉ መለሰች፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ የነበሩትን ሙታን መለሱ፤ ምድርም በውስጥዋ ያሉትን ሙታን መለሰች፤ ሁሉም እንደ ሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።

[14] ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ፤ ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።

[15] በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ የማይገኘውም ሁሉ በእሳት ባሕር ውስጥ ይጣላል።

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters