Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:18

[1] “ለሰርዴስም ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍለት ፥ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል ፥ ሥራህን አውቃለሁ፥ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ፥ ሞተህማል።

[2] እንግዲህ ተግተህ ሊሞቱ የደረሱትን አጽናናቸው፤ በአምላኬ ፊት ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና።

[3] እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ ዐስብ፥ ጠብቀውም፥ ንስሓም ግባ፤ ባትተጋ ግን እንደ ሌባ ድንገት እመጣብሃለሁ፤ በማናቸውም ሰዓት እንደምመጣብህ ከቶ አታውቅም።

[4] ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ፥ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፤ የተገባቸውም ስለሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው፥ ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።

[5] ድል ለነሣውም እንዲህ ያለ ነጭ ልብስ ይገባዋል፤ ስሙም ከሕይወት መጽሐፍ አይደመሰስም፤ በአባቴና በመላክእቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። ሉቃ.

[6] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ።

[7] “ለፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍ ፥ የዳዊት ቤት መክፈቻ ሁሉ በእርሱ ዘንድ ያለ፥ ያለ እርሱ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፥ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል ፥

[8] ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በፊትህ የተከፈተች ደጅ ሰጥቼሃለሁ፤ ሊዘጋት የሚችል የለም፤ ኀይልህ ጥቂት ቢሆንም ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድህም።

[9] እነሆ፥ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ፥ ነገር ግን ከሚዋሹ፥ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ። እነሆም፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ፥ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።

[10] የትዕግሥቴን ቃል ጠብቀሃልና፥ ስለዚህም እኔ በምድር ሁሉ ያሉትን ትፈትናቸው ዘንድ፥ በዓለም ሁሉ ከምትመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።

[11] እነሆ፥ እኔ ቶሎ እመጣለሁ፥ ማንም አክሊልህን የሚወስድብህ እንዳይኖር ያለህን አጽንተህ ያዝ።

[12] ድል የነሣውን በአምላኬ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያ ወዲያም ወደ ውጭ አይወጣም፤ በላዩም የአምላኬን ስምና ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትመጣውን የአዲሲቱን የአምላኬን ከተማ የኢየሩሳሌምን ስም፥ አዲሱንም ስሜን እጽፍበታለሁ።

[13] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ።

[14] “ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን አለቃ እንዲህ ብለህ ጻፍ ፥ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ እግዚአብሔር ከፈጠረው ሁሉ አስቀድሞ የነበረ እንዲህ ይላል።

[15] በራድ፥ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፤ በራድ፥ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር።

[16] እንዲሁ ለብ ስላልህ፥ በራድም፥ ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።

[17] ሀብታም ነኝና፥ ባለጠጋ ሆኛለሁ፥ አንድ ስንኳ አያስፈልገኝም ትላለህ። ነገር ግን ጐስቌላና ምስኪን፥ ድሃም፥ ዕውርም፥ የተራቈትህም መሆንህን አታውቅም።

[18] ስለዚህ ባለጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኀፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳለውን ኵuል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እነግርሃለሁ።

[19] እኔ የምወዳቸውን እገሥጻቸዋለሁ፤ አስተምራቸዋለሁም፤ እንግዲህ ቅና፤ ንስሓም ግባ።

[20] እነሆ፥ እኔ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ድምፄንም ሰምቶ የሚከፍትልኝ ቢኖር ያንጊዜ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።

[21] እኔ ድል እንደ ነሣሁ፥ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደ ተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።

[22] መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ዦሮ ያለው ይስማ።”

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters