Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:38

[1] ከዚህም በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከፊቱ ብርሃንና ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች።

[2] በብርቱ ድምፅም ፥ “ታላቂቱ ሀገር ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፤ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፥ የርኩሳንና የተጠሉ ወፎች ሁሉና የርኩስ አውሬ ሁሉ መኖሪያም ሆነች።

[3] አሕዛብ ሁሉ ከዝሙቷ ቅWጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋልና፤ የምድር ነገሥታትም ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ፥ የምድር ነጋዴዎችም ከቅምጥልነቷ ኀይል የተነሣ ባለጠጋዎች ሆኑ ” ብሎ ጮኸ።

[4] ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ፤ እንዲህ ሲል ፥ “ሕዝቤ ሆይ፥ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፥ ከመቅሠፍቷም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።

[5] ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዐመፅዋን አስቦባታልና።

[6] እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡላት፤ በቀዳችበትም ጿ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቅዱላት።

[7] የበደለችውንና፥ የተደላደለችውንም ያህል እንዲሁ መከራ አጽኑባት፤ አስለቅሱአትም፤ በልብዋ ፥ ለዘለዓለም እነግሣለሁ፤ መበለትም አልሆንም፤ ኀዘንም አላይም ብላ ነበርና።

[8] ስለዚህ በአንድ ጊዜ ሞትና ኀዘን፥ ራብም የሆኑ መቅሠፍቶችዋ ይመጡባታል፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ኀያል ነውና።

[9] “ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት፥ የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ፥ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ።

[10] ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ ከሩቅ ቆመው ፥ ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱዪቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና’ እያሉ ይናገራሉና።

[11] የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና፤

[12] ወርቁንም፥ ብሩንም፥ የከበረውንም ዕንቐ፥ ሉሉንም፥ ነጭ ሐሩንም፥ ብጫ ሐሩንም፥ ቀይ ሐሩንም፥ ሰማያዊ ሐሩንም፥ የዞጲ ዕንጨቱንም፥ ከዝሆን ጥርስ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ፥ የከበረ ዕንቐ ያለበትን ጌጣ ጌጥ ሁሉ፥ ናሱንና፥ ብረቱን፥ ቀይና ነጭ ዕብነ በረዱንም፥

[13] ቀናንሞዉንና አበሞዉን ዕጣኑንና፥ ሜሮኑን፥ ደቃቅ ዕጣኑን፥ ወይኑንና ፥ ዘይቱን፥ ስንዴውንና ዱቄቱን፥ ከብቱንና ፥ በጉን ፥ ፈረሱንና፥ ሠረገላውንም፥ ባሪያዎችንና የሰው ነፍሳትንም የሚገዛ የለምና።

[14] “ነፍስሽም የጐመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፤ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም።

[15] እነዚህን የነገዱ፥ በእርስዋም ባለጠጋዎች የሆኑ፥ ሥቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው ያለቅሱላታል፤ “ዋይ፥ ዋይም ” ይሉላታል።

[16] እንዲህም ይላሉ ፥ ነጭ ሐርና ብጫ ሐር፥ ቀይ ሐርም ለለበሰችው፥ በወርቅና በከበረ ዕንቐ፥ በአልማዝም ለተሠራችው ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ባለጠግነቷ በአንድ ሰዓት ትጠፋለችና።

[17] የመርከብ መሪ ሁሉ፥ የመርከብም ጠበብት ሁሉ፥ መርከበኟችም፥ በባሕር ላይ የሚሠሩ ሁሉም ከሩቁ ቆሙ።

[18] የሀገሪቱንም መቃጠል ባዩ ጊዜ ፥ ይህቺን ታላቅ ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች እያሉ ጮሁ።

[19] በራሳቸው ላይም ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለጸግነቷ የተነሣ ባለጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ።

[20] ሰማይ ሆይ፥ ቅዱሳን ነቢያት፥ ሐዋርያትም ሆይ፥ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።”

[21] አንድ ብርቱ መልአክም እንደ ወፍጮ ያለ ታላቅ ድንጋይ ፈነቀለና፥ ወደ ባሕር ወረወረው፤ እንዲህም አለ ፥ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተፈንቅላ ትወድቃለች፤ እንግዲህም አትገኝም።

[22] በውስጥዋም የመሰንቆ ድምጽ አይሰማም፤ የእንዚራ፥ የዘፈንና የመለከት ድምፅም በእርስዋ አይሰማም፤ በውስጥዋም ሥራ ሁሉ፥ ሠራተኛም ሁሉ አይገኝም፤ በውስጥዋም የወፍጮ ድምፅ የለም፤

[23] የመብራት ወገግታም የለም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱ ድምፅም አይሰማባትም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መሳፍንቶች ናቸውና፤ የምድር አሕዛብንም ሁሉ በአስማትሽ አስተሻልና።

[24] የነቢያት ደም፥ የቅዱሳንም፥ በክርስቶስ ስም በምድር ላይ የተገደሉ የሰማዕታትም ሁሉ ደም በአንቺ ላይ ተገኝቶአልና።”

የዮሐንስ ራእይ። የዮሐንስ ራእይ — Chapters