[1] በእኛ ዘንድ የተፈጸመውንና የታመነውን የሥራውን ዜና በሥርዐት ሊጽፉ የጀመሩ ብዙዎች ናቸው።
[2] ከእኛ አስቀድሞ በዐይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩ እንደ አስተላለፉልን፤
[3] የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው ተከትዬ፥ ሁሉንም በየተራው እውነተኛውን እጽፍልህ ዘንድ መልካም ሁኖ ታየኝ።
[4] የተማርኸውን የነገሩን እውነት ጠንቅቀህ ታውቅ ዘንድ።
[5] በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ።
[6] ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ሥርዐትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ።
[7] ልጅም አልነበራቸውም፤ ኤልሳቤጥ መካን ነበረችና፤ ሁለቱም አርጅተው ነበር፤ ዘመናቸውም አልፎ ነበር።
[8] እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራው የክህነትን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ፥
[9] ካህናት እንደሚያደርጉት የሚያጥንበት ጊዜ ደረሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ።
[10] ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸልዩ ነበር።
[11] የእግዚአብሔር መልአክም በዕጣን መሠውያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው።
[12] ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ ፍርሀትም ረዓድም ወረደበት።
[13] መልአኩም እንዲህ አለው ፥ “ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።
[14] ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።
[15] እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል።
[16] ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል።
[17] እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም ዐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኀይል በፊቱ ይሄዳል።”
[18] ዘካርያስም የእግዚአብሔርን መልአክ እንዲህ አለው ፥ “ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅቼአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል።”
[19] መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ።
[20] አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል።”
[21] ሕዝቡ ግን ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ዘግይቶ ነበርና እጅግ ተደነቁ።
[22] ወደ እነርሱ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜም እነርሱን ማነጋገር ተሳነው፤ በቤተ መቅደስም የተገለጠለት እንዳለ ዐወቁ፤ እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመለከታቸው ኖረ።
[23] ከዚህም በኋላ የማገልገሉ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ።
[24] ከእነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ፅንስዋንም ለአምስት ወር ሸሸገች፤ እንዲህ ስትል ፥
[25] “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ በጐበኘኝ ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ።”
[26] በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስሟ ናዝሬት ወደምትባለው ወደ አንዲት የገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሚሆን ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨችው ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፤
[27] የዚያችም ድንግል ስምዋ ማርያም ይባል ነበረ።
[28] መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ ፥ “ደስ ያለሽ፥ ጸጋንም የተመላሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ” አላት።
[29] እርስዋም በአየችው ጊዜ ከአነጋገሩ የተነሣ ደነገጠችና “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ብላ ዐሰበች።
[30] መልአኩም እንዲህ አላት ፥ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ።
[31] እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ።
[32] እርሱም ታላቅ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።
[33] ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለሙ ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”
[34] ማርያምም መልአኩን ፥ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” አለችው።
[35] መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት ፥ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል።
[36] እነሆ፥ ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን ኤልሣቤጥም እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል የነበረችው ከፀነሰች እነሆ፥ ይህ ስድስተኛ ወር ነው።
[37] ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና”።
[38] ማርያምም መልአኩን ፥ “እነሆኝ፥ የእግዚአብሔር ባሪያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” አለችው፤ ከዚህ በኋላም መልአኩ ከእርስዋ ዘንድ ሄደ።
[39] በዚያም ወራት ማርያም ፈጥና ተነሣች፤ ወደ ተራራማው ሀገር ወደ ይሁዳ ከተማም ደረሰች።
[40] ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሣቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት።
[41] ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ዘለለ፤ በኤልሣቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት።
[42] በታላቅ ቃልም ጮሃ እንዲህ አለች ፥ “ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው።
[43] የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ?
[44] እነሆ፥ ሰላምታ ስትሰጭኝ ቃልሽን በሰማሁ ጊዜ፥ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።
[45] ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽ ቃል እንደሚሆን የምታምኚ አንቺ ብፅዕት ነሽ።”
[46] ማርያምም እንዲህ አለች ፥ “ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች።
[47] ልቡናዬም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሐሤት ታደርጋለች።
[48] የባርያውን ትሕትና ተመልክቶአልና። እነሆ፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል።
[49] ታላቅ ሥራን ሠርቶልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።
[50] ይቅርታውም ለሚፈሩት ለልጅ ልጅ ነው።
[51] በክንዱ ኀይልን አደረገ፤ በልባቸው ዐሳብ የሚታበዩትንም በተናቸው።
[52] ኀያላኑን ከዙፋናቸው አዋረዳቸው፤ ትሑታኑንም ከፍ ከፍ አደረጋቸው።
[53] የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው፤ ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው።
[54] ብላቴናውን እስራኤልን ተቀበለው፤ ይቅርታውንም ዐሰበ።
[55] ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ እስከ ዘለዓለም እንደ ተናገረው።”
[56] ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚህ በኋላም ወደ ቤቷ ተመለሰች።
[57] የኤልሣቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች።
[58] ዘመዶችዋና ጎረቤቶችዋም እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው።
[59] ከዚህም በኋላ በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገዝሩት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት።
[60] እናቱ ግን መልሳ ፥ “አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ ” አለች።
[61] እነርሱም ፥ “ከዘመዶችሽ ስሙ እንደዚህ የሚባል የለም ” አሉአት።
[62] አባቱንም ጠቅሰው ፥ “ማን ሊሉት ትወዳለህ?” አሉት።
[63] ብራናም ለመነና “ስሙ ዮሐንስ ይባል ” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደነቁ።
[64] ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ።
[65] በዚያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍርሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይሁዳ በተራራማው ሀገር ሁሉ ተወራ።
[66] የሰሙትም ሁሉ ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና።
[67] በአባቱ በዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ መላበት፤ እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረ ፥
[68] “ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤
[69] ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤
[70] ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን በነቢያት አፍ እንደ ተናገረ።
[71] ከጠላቶቻችን እጅ፥ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ።
[72] ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ።
[73] ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ያስብ ዘንድ።
[74] ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሀት፥
[75] በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ በዘመናችን ሁሉ እንድናመልከው ይሰጠን ዘንድ።
[76] አንተም ሕፃን፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ትጠርግ ዘንድ በፊቱ ትሄዳለህና።
[77] ኀጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ መድኀኒታቸውን እንዲያውቁ ለአሕዛብ ትሰጣቸው ዘንድ።
[78] ከአርያም በጐበኘን በአምላካችን በይቅርታውና በቸርነቱ።
[79] በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩት ብርሃኑን ያሳያቸው ዘንድ፥ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።”
[80] ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸና፤ ለእስራኤልም እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።