Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:02

[1] ዘወትር እንዲጸልዩ፥ እንዳይሰለቹም በምሳሌ ነገራቸው።

[2] እንዲህም አላቸው ፥ “በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ፥ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበር።

[3] በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ ዕለት ዕለትም ወደ እርሱ እየመጣች ከባለጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር።

[4] እንቢ ብሎም አዘገያት። ከዚህም በኋላ በልቡ ዐስቦ እንዲህ አለ ፥ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፥ ሰውንም ባላፍር

[5] ይህቺ ሴት እንዳትዘበዝበኝ፥ ዘወትርም እየመጣች እንዳታታክተኝ እፈርድላታለሁ’።”

[6] ጌታችንም እንዲህ አላቸው ፥ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።

[7] እንግዲህ እግዚአብሔር በመዓልትና በሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለወዳጆቹ አይፈርድምን? ወይስ ቸል ይላቸዋልን?

[8] እላችኋለሁ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆን?”

[9] ራሳቸውን ለሚያመጻድቁና ባልንጀራቸውን ለሚንቁ እንዲህ ብሎ መሰለላቸው።

[10] “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ፥ ሁለተኛውም ቀራጭ ነበር።

[11] ፈሪሳዊውም ቆመና እንዲህ ብሎ ጸለየ ፥ ‘አቤቱ እንደ ሌሎች ሰዎች፥ እንደ ቀማኟችና እንደ ዐመፀኟች፥ እንደ አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ያላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ።

[12] እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጿማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ከዐሥር አንድ እሰጣለሁ።’

[13] ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዐይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱንም እየመታ ፥ ‘አቤቱ፥ እኔን ኀጢኣተኛውን ይቅር በለኝ ’ አለ።

[14] እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ይከብራልና።”

[15] ይባርካቸውም ዘንድ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው።

[16] ጌታችን ኢየሱስም ጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው ፥ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው፥ አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።

[17] እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃናት ያልተቀበላት አይገባባትም።”

[18] አንድ አለቃም ፥ “ቸር መምህር፥ ምን ሥራ ሠርቼ የዘለዓለም ሕይወትን እወርሳለሁ?” አለው።

[19] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር የለም።

[20] ትእዛዛቱን አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ ‘አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህንም አክብር።’

[21] እርሱም ፥ ‘ይህንስ ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ጠብቄአለሁ’።” አለው።

[22] ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ አለው ፥ “አንዲት ቀርታሃለች፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለነዳያን ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ።”

[23] እርሱ ግን ይህን ሰምቶ በጣም አዘነ፤ እርሱ እጅግ ባለጸጋ ነበርና።

[24] ጌታችን ኢየሱስም እጅግ ሲያዝን አይቶ እንዲህ አለ ፥ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው!

[25] ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊያልፍ ይቀላል።”

[26] የሰሙትም ፥ “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።

[27] እርሱ ግን “በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል ” አላቸው።

[28] ጴጥሮስም ፥ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” አለው።

[29] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ቤቱንና ዘመዶቹን፥ ወንድሞቹንና ሚስቱን፥ ልጆቹንም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የሚተው፥

[30] በዚህ ዓለም መቶ እጥፍ ዋጋ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወትን የማይቀበል ማንም የለም።”

[31] ዐሥራ ሁለቱንም ወሰዳቸው፤ እንዲህም አላቸው ፥ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ በነቢያትም የተጻፈው ሁሉ በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል።

[32] ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱበታልም፤ ይሰድቡታልም፤ ይተፉበታልም።

[33] ይገርፉታል፤ ይገድሉታልም፤ በሦስተኛዪቱም ቀን ይነሣል።”

[34] እነርሱ ግን፤ ከተናገራቸው ያስተዋሉት የለም፤ ይህ ነገር ከእነርሱ የተሰወረ ነበርና፤ የተናገረውንም አያውቁም ነበርና።

[35] ከዚህም በኋላ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜ አንድ ዕውር በጎዳና ተቀምጦ ይለምን ነበር።

[36] የሚያልፈውንም ሰው ድምፅ ሰምቶ ፥ “ይህ የምሰማው ምንድን ነው?” አለ።

[37] እነርሱም ፥ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል ” ብለው ነገሩት።

[38] ድምፁንም ከፍ አድርጎ ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ ” አለ።

[39] የሚመሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን በጣም ጮኾ ፥ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ ” አለ።

[40] ጌታችን ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ።

[41] ወደ እርሱም በደረሰ ጊዜ ፥ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ፥ “ጌታ ሆይ፥ ዐይኖቼ እንዲያዩ ነው ” አለው።

[42] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እይ፤ እምነትህ አዳነችህ ” አለው።

[43] በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤ ተከተለውም፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters