[1] በዚያ ወራትም ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ቀላቀለው ስለ ገሊላ ሰዎች ነገሩት።
[2] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ይህች መከራ ስለ አገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለይተው ኀጢኣተኟች የሆኑ ይመስሉአችኋልን?
[3] አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።
[4] ወይስ እነዚያ በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ የገደላቸው ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኀጢእታኟች ይመስሉአችኋልን?
[5] አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።”
[6] እንዲህም ብሎ መሰለላቸው ፥ “አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሄዶ አላገኘም።
[7] የወይኑን ጠባቂም ፥ “የዚችን በለስ ፍሬ ልወስድ ስመላለስ እነሆ፥ ሦስት ዓመት ነው፤ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቐረጣት ” አለው።
[8] እርሱም መልሶ እንዲህ አለው ፥ “አቤቱ አፈር ቈፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፥ ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ የዘንድሮን እንኳ ተዋት።
[9] ምናልባት ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፥ ያለዚያ ግን እንቈርጣታለን።”
[10] በሰንበትም በአንድ ምኵuራብ ውስጥ አስተማራቸው።
[11] ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ ጋኔን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ ጐባጣም ነበረች፤ ከቶ ቀጥ ብላ መቆም አትችልም ነበር።
[12] ጌታችን ኢየሱስም አይቶ ራራላት፥ ጠርቶም ፥ “ሴትዮ፥ ከደዌሽ ተፈትተሻል ” አላት።
[13] እጁንም በላይዋ ጫነ፤ ያንጊዜም ፈጥና ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።
[14] የምኵuራቡ ሹምም ጌታ ኢየሱስ በሰንበት ፈውሶአልና፤ እየተቈጣ መልሶ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው ፥ “ሥራችሁን የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች ያሉ አይደለምን? ያንጊዜ ኑና ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም።”
[15] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አላቸው ፥ “እናንት ግብዞች፥ እናንተሳ አህያችሁን ወይም በሬአችሁን በሰንበት ቀን ገለባ ከሚበላበት አትፈቱትምን? ውኃ ልታጠጡትስ አትወስዱትምን?
[16] ይህቺ የአብርሃም ልጅ እነሆ፥ ሰይጣን ከአሰራት ዐሥራ ስምንት ዓመት ነው፤ እርስዋስ በሰንበት ቀን ከእስራቷ ልትፈታ አይገባምን?”
[17] ይህንም ባለ ጊዜ በእርሱ ላይ በጠላትነት የተነሡበት ሁሉ አፈሩ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከእርሱ ስለሚደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ደስ አላቸው።
[18] በዚያ ቀንም ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው ፥ “መንግሥተ ሰማያት ምን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ?
[19] ሰው ወስዶ በእርሻ ውስጥ የዘራት የሰናፍጭ ቅንጣትን ትመስላለች፤ አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ውስጥ ተጠለሉ።”
[20] ዳግመኛም እንዲህ አለ ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ?
[21] ሴት ወስዳ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት የለወሰችበትን፥ ሁሉንም እንዲቦካ ያደረገውን እርሾ ትመስላለች”።
[22] በየከተማውና በየመንደሩ እየሄደ፥ በኢየሩሳሌምም እየተመላለሰ ያስተምር ነበር።
[23] አንድ ሰውም ፥ “አቤቱ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው ፥
[24] “ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ፤ እላችኋለሁ፥ ሊገቡ የሚሹ ብዙዎች ናቸው፤ ግን አይችሉም።
[25] ባለቤቱ ተነሥቶ ደጁን ይዘጋልና፤ ያንጊዜ ከደጅ ቆመው ፥ ‘አቤቱ፥ አቤቱ፥ ክፈትልን ’ እያሉ በር ሊመቱ ይጀምራሉ፤ መልሶም ፥ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላቸዋል።
[26] ከዚህም በኋላ ፥ በፊትህ በላን፥ ጠጣን፥ በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ።
[27] እርሱም እንዲህ ይላቸዋል ፥ እናንተ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ዐመፅን የምታደርጉ ሁላችሁ፥ ከእኔ ራቁ፤
[28] አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት በአያችኋቸው ጊዜ እናንተን ወደ ውጭ ያወጡአችኋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
[29] ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ፤
[30] ኋለኟች ፊተኟች ይሆናሉ፤ ፊተኟችም ኋለኟች ይሆናሉ።”
[31] በዚያችም ቀን ከፈሪሳውያን ወገን ሰዎች መጥተው ፥ “ከዚህ ውጣና ሂድ፤ ሄሮድስ ሊገድልህ ይሻልና ” አሉት።
[32] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ሂዱና ያችን ቀበሮ እንዲህ በሉአት፤ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ ሕይወትንም አድላለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን እፈጽማለሁ።
[33] ዛሬና ነገስ አለሁ፤ በሦስተኛው ቀን ግን እሄዳለሁ፤ ነቢይ በኢየሩሳሌም እንጂ በውጭ ሊሞት አይገባውምና።
[34] “ነቢያትን የምትገድሊያቸው፥ ወደ አንቺ የተላኩትን ሐዋርያትንም የምትደበድቢያቸው ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፍዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስባቸው ምን ያህል ወደድሁ? ነገር ግን እንቢ አላችሁ።
[35] እነሆ፥ ቤታችሁ ምድረ በዳ ሆኖ ይቀርላችኋል፤ ከዛሬ ወዲያ ‘በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው ’ እስክትሉ ድረስ እንደማታዩኝ እነግራችኋለሁ።”