Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:10

[1] ጌታችን ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው ፥ “መጋቢ የነበረው አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ፤ ገንዘቡን ሁሉ እንደሚበትን አድርገው በእርሱ ዘንድ ከሰሱት።

[2] ጌታውም ጠርቶ ፥ ‘በአንተ ላይ የምሰማው ይህ ነገር ምንድን ነው? እንግዲህ ወዲህ ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ ’ አለው።

[3] ያም መጋቢ ዐስቦ እንዲህ አለ ፥ ‘ምን ላድርግ? አሁን ጌታዬ ከመጋቢነቴ ይሽረኛል፤ ማረስ አልችልም፤ ለመለመንም አፍራለሁ።

[4] እንግዲህ ጌታዬ ከምግብናዬ የሻረኝ እንደ ሆነ በቤታቸው ይቀበሉኝ ዘንድ የማደርገውን እኔ ዐውቃለሁ።’

[5] ለጌታውም ዕዳ የሚከፍሉትን ጠራቸው፤ የመጀመሪያውንም ፥ ‘ለጌታዬ የምትከፍለው ዕዳ ምን ያህል ነው?’ አለው፤ እርሱም ፥ ‘መቶ ማድጋ ዘይት ነው ’ አለው።

[6] ‘እነሆ፥ ደብዳቤህ፤ ተቀምጠህ አምሳ ማድጋ አለብኝ ብለህ ፈጥነህ ጻፍ ’ አለው።

[7] ሁለተኛውንም ፥ ‘አንተሳ ለጌታዬ የምትከፍለው ዕዳ ምን ያህል ነው?’ አለው፤ እርሱም ፥ ‘መቶ ማድጋ ስንዴ ነው ’ አለው፤ ‘እነሆ፥ ደብዳቤህ፤ ተቀምጠህ ሰማንያ አለብኝ ብለህ ፈጥነህ ጻፍ ’ አለው።

[8] ጌታውም ዐመፀኛውን መጋቢ እንደ ብልህ ሰው ስለ ሠራ አመሰገነው፤ ከብርሃን ልጆች ይልቅ የዚህ ዓለም ልጆች በዓለማቸው ይራቀቃሉና።

[9] እኔም እላችኋለሁ ፥ ባለቀባችሁ ጊዜ እነርሱ በዘለዓለም ቤታቸው ይቀበሉአችሁ ዘንድ በዐመፃ ገንዘብ ለእናንተ ወዳጆች አድርጉበት።

[10] “በጥቂት የሚታመን በብዙ ይታመናል፤ በጥቂት የሚያምፅም በብዙም ቢሆን ያምፃል።

[11] በዐመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ በእውነተኛው ገንዘብ ማን ያምናችኋል?

[12] በሌላውስ ገንዘብ ካልታመናችሁ የራሱን ማን ይሰጣችኋል?

[13] ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚችል አገልጋይ የለም፤ ካልሆነም አንዱን ይወድዳል፤ ሁለተኛውንም ይጠላል፤ ወይም ለአንዱ ይታዘዛል፤ ለሁለተኛውም እንቢ ይላል፤ እንዲሁም እናንተ ገንዘብ እየወደዳችሁ ለእግዚአብሔር መገዛት አትችሉም።”

[14] ገንዘብን የሚወዱ ፈሪሳውያንም ይህን ሁሉ ነገር ሰምተው ተጠቃቀሱበት።

[15] እርሱም ፥ “እናንተስ ለሰው ይምሰል ትመጻደቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ልቡናችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ዘንድ የተናቀ ይሆናልና።

[16] “ኦሪትም ነቢያትም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ድረስ ነበሩ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ ይጋፋል።

[17] ነገር ግን ከኦሪት አንዲት ቃል ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል።

[18] “ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ባልዋ የፈታትንም የሚያገባ ያመነዝራል።

[19] “አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ፤ ቀይ ሐርና ነጭ ሐር፥ እጅግም ቀጭን ልብስ ይለብስ ነበር፤ ዘወትርም ተድላና ደስታ ያደርግ ነበር።

[20] በቐስል ሕመም ተይዞ በባለጸጋው ደጅ የወደቀ አልዓዛር የሚባል አንድ ድሃም ነበረ።

[21] ከባለጸጋው ማዕድ የሚወድቀውንም ፍርፋሪ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም እየመጡ ቐስሉን ይልሱት ነበር።

[22] ከዚህም በኋላ ድሃው ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም አጠገብ ወሰዱት፤ ባለጸጋውም ደግሞ ሞተ፤ ተቀበረም፤

[23] በሲኦልም በሥቃይ ሳለ ዐይኖቹን አንሥቶ አብርሃምን ከሩቅ አየው፤ አልዓዛርንም በአጠገቡ ተቀምጦ አየው።

[24] ‘አባት አብርሃም ሆይ፥ እዘንልኝ፤ በዚች እሳት እጅግ ተሠቃይቻለሁና፥ ጣቱን ከውኃ ነክሮ ምላሴን ያቀዘቅዝልኝ ዘንድ አልዓዛርን ላከው ’ ብሎ ተጣራ።

[25] አብርሃም ግን እንዲህ አለው ፥ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ተድላና ደስታ እንዳደረግህ፥ አልዓዛርም እንዲሁ ሁልጊዜ በችጋር እንደ ነበረ ዐስብ፤ አሁን ግን እንዲሁ እርሱ በዚህ ፈጽሞ ተድላና ደስታ ያደርጋል፤ አንተ ግን መከራ ትቀበላለህ።

[26] ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ማለፍ የሚሹ እንዳይችሉ፥ ከእናንተ ወገን የሆኑትም ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል አለ ’

[27] እርሱም እንዲህ አለው ፥ ‘አባት አብርሃም ሆይ፥ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤት እንድትልከው እለምንሃለሁ።

[28] አምስት ወንድሞች ስለ አሉኝ ይንገራቸው፤ እነርሱም ደግሞ ወደዚች የሥቃይ ቦታ እንዳይመጡ ይስሙ።’

[29] አብርሃምም ፥ ‘ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ ’ አለው።

[30] እርሱም ፥ ‘የለም፤ አባት አብርሃም ሆይ፥ ከሙታን አንዱ ወደ እነርሱ ካልሄደና ካልነገራቸው ንስሓ አይገቡም ’ አለው።

[31] አብርሃምም ፥ ‘ሙሴንና ነቢያትን ካልሰሙማ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ቢኖርም እንኳ አይሰሙትም፤ አያምኑትምም ’ አለው።”

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters