[1] ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ።
[2] የካህናት አለቆችና ጻፎችም ሊገድሉት ይሹ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ይፈሩአቸው ነበር።
[3] ቐጥሩ ከዐሥራ ሁለቱ በነበረው በአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ።
[4] ሄዶም ከካህናት አለቆችና ከታላላቆች ጋር እርሱን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ተነጋገረ።
[5] ደስ ብሏቸውም ሠላሳ ብር ሊሰጡት ተስማሙ።
[6] እርሱም እሺ አለ፤ ሰው ሳይኖርም እርሱን አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር።
[7] የፋሲካን በግ የሚያርዱባት የቂጣ በዓልም ደረሰች።
[8] ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ፥ “ሂዱና የምንበላውን የፋሲካ በግ አዘጋጁልን ” አላቸው።
[9] እነርሱም ፥ “ወዴት ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ?” አሉት።
[10] እንዲህም አላቸው ፥ “ወደ ከተማ በገባችሁ ጊዜ፥ የውኃ ማድጋ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደሚገባበትም ቤት እርሱን ተከተሉት።
[11] የዚያን ቤት ጌታ ፥ መምህር ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በግ የምበላበት ቤት ወዴት ነው? ብሎሃል በሉት።
[12] እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።”
[13] በሄዱም ጊዜ እንዳላቸው አገኙ፤ የፋሲካውንም በግ አዘጋጁ።
[14] ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በማዕድ ተቀመጠ፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ተቀመጡ።
[15] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ከመከራዬ አስቀድሞ ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ ወደድሁ።
[16] ነገር ግን፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ እንግዲህ ከእርሱ እንደማልበላ እነግራችኋለሁ ” አላቸው።
[17] ጿውንም ተቀብሎ አመሰገነ፤ እንዲህም አለ ፥ “ይህን እንኩ ሁላችሁም ተካፈሉት።
[18] እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ፤ እንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።”
[19] ኅብስቱንም አነሣ፤ አመስገነ፤ ፈትቶም ሰጣቸው፤ እንዲህም አላቸው ፥ “ስለ እናንተ ቤዛ ሆኖ የሚሰጥ ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤”
[20] እንዲሁም ከእራት በኋላ ጿዉን አንሥቶ እንዲህ አላቸው ፥ “ይህ ጿ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።
[21] “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ በማዕድ ከእኔ ጋር ነው።
[22] የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በእጁ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት።”
[23] ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ ይህን የሚያደርግ ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
[24] ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።
[25] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “አሕዛብን ንጉሦቻቸው ይገዙአቸዋል፤ በላያቸውም ሥልጣን ያላቸው ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ።
[26] ለእናንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቁ እንደ ታናሽ ይሁናችሁ፤ አለቃውም እንደ አገልጋይ ይሁን።
[27] የሚበልጥ ማንኛው ነው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው ነው? ወይስ የሚላላከው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው አይደለምን? እነሆ፥ እኔ በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ።
[28] ነገር ግን ስለ እኔ የታገሣችሁ እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ናችሁ።
[29] አባቴ ለእኔ እንደ ሰጠኝ፥ እኔም ለእናንተ መንግሥትን አዘጋጅላችኋለሁ፤
[30] በመንግሥቴ በማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በወንበሮችም ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዱ ዘንድ።”
[31] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ ፥ “ስምዖን፥ ስምዖን ሆይ፥ ሰይጣን እንደ አጃ ሊያበጥራችሁ አሁን ልመናን ለመነ።
[32] እኔ ግን ሃይማኖታችሁ እንዳይደክም ስለ እናንተ ጸለይሁ፤ አንተም ተመልሰህ ወንድሞችህን አጽናቸው።”
[33] እርሱም ፥ “አቤቱ፥ እኔ ለመታሰርም ቢሆን፥ ለሞትም ቢሆን እንኳ ከአንተ ጋራ ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ ” አለው።
[34] እርሱ ግን ፥ “ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ እንደማታውቀኝ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ” አለው።
[35] ደግሞም ፥ “ያለ ስልቻ፥ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ በውኑ የተቸገራችሁት ነገር ነበርን?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “የለም ” አሉት።
[36] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “አሁን ግን ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ ያድርግ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ።
[37] እላችኋለሁ፥ ከኃጥኣን ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ይደርሳል፤ ስለ እኔ የተጻፈውም ሁሉ ይፈጸማል።”
[38] እነርሱም ፥ “አቤቱ፥ እነሆ፥ እዚህ በእኛ ዘንድ ሁለት ሰይፎች አሉ ” አሉት፤ እርሱም ፥ “እንግዲያስ ይበቃችኋል ” አላቸው።
[39] ወጥቶም እንዳስለመደው ይጸልይ ዘንድ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
[40] ከዚያም ደርሶ ፥ “ወደ መከራ እንዳትገቡ ጸልዩ ” አላቸው።
[41] የድንጋይ ውርወራ ያህልም ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ እየሰገደ ጸለየ።
[42] እንዲህም አለ ፥ “አባት ሆይ፥ ብትፈቅድስ ይህን ጿ ከእኔ አሳልፈው፤ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።”
[43] የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው።
[44] ፈራ፤ መላልሶም ጸለየ፤ ላቡም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆነ።
[45] ከሚጸልይበትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ፤ ከኀዘንም የተነሣ ተኝተው አገኛቸው።
[46] “ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ ” አላቸው።
[47] ይህንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳም ይመራቸው ነበር፤ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸውም ምልክት ይህ ነበር፤ “የምስመው እርሱ ነውና እርሱን አጽንታችሁ ያዙት ” አላቸው።
[48] ጌታችን ኢየሱስም ይሁዳን ፥ “በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?” አለው።
[49] አብረውት የነበሩትም የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ጌታችን ኢየሱስን ፥ “አቤቱ፥ በሰይፍ ልንመታቸው ትፈቅዳለህን?” አሉት።
[50] ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው፤ ቀኝ ጆሮውንም ቈረጠው።
[51] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “ይህንስ ተው ” አለ፤ ወዲያውም ጆሮውን ዳስሶ አዳነው።
[52] ጌታችን ኢየሱስም ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፥ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው ፥ “ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን?
[53] ዘወትርም ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስ ስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፤ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው።”
[54] ይዘውም ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት ወሰዱት፤ ጴጥሮስም ከሩቅ ይከተለው ነበር።
[55] በግቢውም ውስጥ እሳት አንድደው ተቀመጡ፤ ጴጥሮስም አብሮአቸው በመካከላቸው ተቀመጠ።
[56] በእሳቱም ብርሃን በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ብላቴና አየችው፤ እርሱ መሆኑንም ለየችውና ፥ “ይህም ከእርሱ ጋር ነበር ” አለች።
[57] እርሱ ግን ፥ “ሴትዮ! የምትዪውን አላውቅም ” ብሎ ካደ።
[58] ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አየውና ፥ “አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ ” አለው፤ ጴጥሮስ ግን ፥ “አንተ ሰው! እኔ አይደለሁም ” አለው።
[59] አንዲት ሰዓት ያህልም ቈይቶ አንድ ሌላ ሰው ፥ “ይህም በእውነት ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ሰውየውም የገሊላ ሰው ነው ” ብሎ አስጨነቀው።
[60] ጴጥሮስ ግን ፥ “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም ” አለው፤ እርሱም ይህን ሲናገር ያንጊዜ ዶሮ ጮኸ።
[61] ጌታችን ኢየሱስም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፤ ጴጥሮስም ፥ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ” ያለውን የጌታችንን ቃል ዐሰበ።
[62] ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶን አለቀሰ።
[63] ጌታችን ኢየሱስን ይዘውት የነበሩት ሰዎችም ይዘባበቱበትና ይደበድቡት ነበር።
[64] ሸፍነውም ፊቱን በጥፊ ይመቱት ነበር፤ “ፊትህን በጥፊ የመታህ ማነው? ንገረን ” እያሉም ይጠይቁት ነበር።
[65] ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር።
[66] በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት።
[67] “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን ” አሉት፤ እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም።
[68] ብጠይቃችሁም አትመልሱልኝም፤ ወይም አትተዉኝም።
[69] ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።”
[70] ሁሉም ፥ “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት፤ እርሱም ፥ “እኔ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ ” አላቸው።
[71] እነርሱም ፥ “ስለ እርሱ ምን ምስክር እንሻለን? እኛ ራሳችን ሲናገር ሰምተናል ” አሉ።