[1] ብዙ ሰዎችም በእርሱ ዘንድ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ይሰሙ ነበር፤ እርሱ ግን በጌንሴሬጥ ባሕር ወደብ ቁሞ ነበር።
[2] በባሕሩም ዳር ሁለት ታንኳዎች ቁመው አየ፤ ከእነርሱም ውስጥ ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን ሊያጥቡ ወረዱ።
[3] ከሁለቱ ታንኳዎች ወደ አንዲቱ ታንኳ ወጣ፤ ይቺውም ታንኳ የስምዖን ነበረች፤ “ከምድር ጥቂት እልፍ አድርጋት ” አለው፤ በታንኳዪቱም ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን አስተማራቸው።
[4] ትምህርቱንም ከፈጸመ በኋላ ስምዖንን ፥ “ወደ ጥልቁ ባሕር ፈቀቅ በል፤ መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ ” አለው።
[5] ስምዖንም መልሶ ፥ “መምህር፥ ሌሊቱን ሁሉ ደክመናል፤ የያዝነውም የለም፤ ነገር ግን ስለ አዘዝኸን መረቦቻችንን እንጥላለን ” አለው።
[6] እንዳዘዛቸውም ባደረጉ ጊዜ፥ መረቡ እስኪቀደድ ድረስ ብዙ ዓሣ ተያዘ።
[7] መጥተውም ይረዱአቸው ዘንድ በሌላ ታንኳ የነበሩትን ባልንጀሮቻቸውን ጠሩ፤ መጥተውም እስኪጠልቁ ድረስ ሁለቱን ታንኳዎች ሞሉ።
[8] ስምዖን ጴጥሮስም ይህን አይቶ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና ፥ “እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና አቤቱ ከእኔ ፈቀቅ በል፤” አለው።
[9] እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ስለ ተያዘው ዓሣ ተደንቀው ነበርና።
[10] እንዲሁም የስምዖን ባልንጀራዎች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ተደነቁ፤ ጌታችን ኢየሱስም ስምዖንን ፥ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህስ ሰውን ታጠምዳለህ ” አለው።
[11] ታንኳዎቻቸውንም ወደ ምድር አወጡና ሁሉን ትተው ተከተሉት።
[12] በአንዲት ከተማ ሳለም ሁለመናው ለምጻም የሆነ ሰው መጣ፤ ጌታችን ኢየሱስንም ባየው ጊዜ በፊቱ ወድቆ ሰገደለትና ፥ “አቤቱ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ” እያለ ማለደው።
[13] እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና ፥ “እወዳለሁ ንጻ ” አለው፤ ያንጊዜም ለምጹ ለቀቀው።
[14] ለማንም እንዳይናገር ከለከለው፤ “ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አስመርምር፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ ነጻህ ሙሴ እንደ አዘዘ መባህን አቅርብ ” ብሎ አዘዘው።
[15] ዜናውም በሁሉ ተሰማ፤ ብዙ ሰዎችም ትምህርቱን ሊሰሙ፥ ከደዌአቸውም ሊፈወሱ ይመጡ ነበር።
[16] እርሱ ግን ወደ ምድረ በዳ እየወጣ ይጸልይ ነበር።
[17] ከዚህም በኋላ፥ ከዕለታት በአንድ ቀን ሲያስተምራቸው እንዲህ ሆነ፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች፥ ከኢየሩሳሌምም የመጡ ፈሪሳውያንና የኦሪት መምህራን ነበሩ፤ እርሱም ይፈውስ ዘንድ የእግዚአብሔር ኀይል ነበረ።
[18] እነሆ፥ ሰዎች በአልጋ ተሸክመው ሽባ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እንዲፈውሰውም ወደ እርሱ ሊያስገቡት ወደዱ።
[19] ሰውም ተጨናንቆ ነበርና የሚያስገቡበት አጡ፤ ወደ ሰገነትም ወጡ፤ ጣራውንም አፍርሰው ወደ ቤቱ ውስጥ በጌታችን በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት።
[20] እምነታቸውንም አይቶ ያን ሰው ፥ “ኀጢአትህ ተሰረየልህ ” አለው።
[21] ጻፎችና ፈሪሳውያንም ፥ “የሚሳደብ ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ማስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር።
[22] ጌታችን ኢየሱስም የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው ፥ “በልባችሁ ምን ታስባላችሁ?
[23] ኀጢአትህ ተሰረየልህ ከማለትና ተነሥተህ ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
[24] ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ ያን ሽባ ፥ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ ብዬሃለሁ ” አለው።
[25] ያንጊዜም ተነሥቶ ተኝቶበት የነበረውን አልጋ በፊታቸው ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።
[26] ሁሉም ተደነቁ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፤ እጅግም እየፈሩ ፥ “ዛሬ ድንቅ ነገር አየን ” አሉ።
[27] ከዚህም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ ሰው በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየና ፥ “ተከተለኝ ” አለው።
[28] ሁሉንም ተወና ተነሥቶ ተከተለው።
[29] ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ብዙ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከእርሱም ጋር ለምሳ ተቀምጠው የነበሩ ቀራጮችና ኀጢአተኟች፥ ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ።
[30] ጻፎችና ፈሪሳውያንም ፥ “ከቀራጮችና ከኃጥኣን ጋር ለምን ትበላላችሁ? ትጠጡማላችሁ?” ብለው በደቀ መዛሙርቱ ላይ አንጐራጐሩ።
[31] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “ባለ መድኀኒትን በሽተኟች እንጂ ጤነኟች አይሹትም።
[32] ኃጥኣንን ወደ ንስሓ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።”
[33] እነርሱም ፥ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለምን በብዙ ይጿማሉ? ጸሎትስ ስለምን ያደርጋሉ? የፈሪሳውያን ወገኖች የሆኑትም ስለምን እንዲሁ ያደርጋሉ? ያንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን ይበላሉ? ይጠጣሉም?” አሉት።
[34] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጿም አይችሉም።
[35] ነገር ግን ሙሽራውን ከእነርሱ የሚወስዱበት ቀን ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጿማሉ።”
[36] በምሳሌም እንዲህ አላቸው ፥ “በአሮጌ ልብስ ቀዳዳ ላይ የአዲስ ልብስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ያለዚያ ግን አዲሱ አሮጌውን ይቀድደዋል፤ አዲሱ እራፊም ከአሮጌው ጋር አይስማማም።
[37] አዲስ ጠጅንም በአሮጌ ረዋት የሚያደርግ የለም፤ ያለዚያ ግን ይቀድደዋል፤ ወይኑም ይፈስሳል፤ ረዋቱም ይቀደዳል።
[38] ነገር ግን አዲሱን ጠጅ በአዲስ ረዋት ያደርጉታል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠባበቃሉ።
[39] የከረመውን የወይን ጠጅ ሊጠጣ ወድዶ አዲሱን የሚሻ የለም፤ የከረመው ይሻላል ይላልና።”