[1] ቀራጮችና ኀጢኣተኟችም ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር።
[2] ጻፎችና ፈሪሳውያንም ፥ “ይህስ ኀጢኣተኟችን ይቀበላል፤ አብሮአቸውም ይበላል ” ብለው አንጐራጐሩ።
[3] እንዲህም ብሎ መሰለላቸው።
[4] “ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት ሰው ቢኖር፥ ከእነርሱ አንዲቱ ብትጠፋው ዘጠና ዘጠኙን በምድረ በዳ ትቶ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋት ዘንድ ወደ ጠፋችው ይሄድ የለምን?
[5] በአገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ላይ ይሸከማታል።
[6] ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ፥ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን ጠርቶ ፥ የጠፋችኝን በጌን አግኝቼአታለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል።
[7] እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢኣተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል።
[8] “ዐሥር ድሪም ያላት ሴት ብትኖር፥ አንዲቱ ብትጠፋባት መብራት አብርታ በቤቷ ያለውን ሁሉ እየፈነቀለች እስክታገኛት ድረስ ተግታ ትፈልግ የለምን?
[9] ያገኘቻት እንደ ሆነም ወዳጆችዋንና ጎረቤቶችዋን ጠርታ ፥ ‘የጠፋችኝን ድሪሜን አግኝቼአታለሁና፥ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ’ ትላቸዋለች።
[10] እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢኣተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል።”
[11] ዳግመኛም እንዲህ አለ ፥ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።
[12] ታናሹ ልጁም አባቱን ፥ ‘አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ከፍለህ ስጠኝ ’ አለው፤ ገንዘቡንም ከፍሎ ሰጠው።
[13] ከጥቂት ቀን በኋላም ያ ትንሹ ልጁ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ በዚያም በመዳራት እየኖረ ገንዘቡን ሁሉ በተነ፤ አጠፋም።
[14] ገንዘቡንም ሁሉ በጨረሰ ጊዜ፥ በዚያ ሀገር ጽኑ ራብ መጣ፤ እርሱም ተቸገረ።
[15] ሄዶም ከዚያ ሀገር ሰዎች ለአንዱ ተቀጠረ፤ እሪያዎችንም ይጠብቅ ዘንድ ወደ እርሻው ቦታ ሰደደው።
[16] እሪያዎች ከሚመገቡት ተረንቃሞም ይጠግብ ዘንድ ተመኘ፤ ግን የሚሰጠው አልነበረም።
[17] በልቡም እንዲህ ብሎ ዐሰበ ፥ እህል የሚተርፋቸው የአባቴ ሠራተኟች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረኃብ ልሞት ነው።
[18] ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና እንዲህ ልበለው ፥ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ።
[19] እንግዲህ ወዲህስ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።’
[20] ተነሥቶም ወደ አባቱ ሄደ፤ አባቱም ከሩቅ አየውና ራራለት፤ ሮጦም አንገቱን አቅፎ ሳመው።
[21] ልጁም ፥ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ ’ አለው።
[22] አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው ፥ ‘ያማሩ ልብሶችን ቶሎ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱም ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤’
[23] የሰባውን ፍሪዳም አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ ደስም ይበለን።
[24] ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአልና ደስ ይላቸውም ጀመር።
[25] “ታላቁ ልጁም በእርሻ ነበርና ተመልሶ ወደ ቤቱ አጠገብ በደረሰ ጊዜ የዘፈኑንና የመሰንቆውን ድምፅ ሰማ።
[26] ከአባቱ ብላቴኖችም አንዱን ጠርቶ ፥ ‘ይህ የምሰማው ምንድን ነው?’ አለው።
[27] እርሱም ፥ ‘ወንድምህ ከሄደበት መጣ፤ አባትህም የሰባውን ፍሪዳ አረደ፤ በሕይወት አግኝቶታልና ’ አለው።
[28] ተቈጥቶም ‘አልገባም ’ አለ፤ አባቱም ወጥቶ ማለደው።
[29] መልሶም አባቱን እንዲህ አለው ፥ ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት ተገዛሁልህ፤ ፈጽሞ ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ ለእኔ ግን ከባልንጀሮቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ የፍየል ጠቦት እንኳ አልሰጠኸኝም።
[30] ከአመንዝሮች ጋር ገንዘብህን ሁሉ የጨረሰ ይህ ልጅህ በተመለሰ ጊዜ ግን የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’
[31] አባቱም እንዲህ አለው ፥ ‘ልጄ አንተማ እኮ ዘወትር ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው።
[32] ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ተገኝቶአልና፥ ደስ ሊለን፥ ሐሤትም ልናደርግ ይገባል።”