Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 9:58

[1] ዐሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት ጠራና ፥ በአጋንንት ሁሉ ላይ፥ ድውያንንም ይፈውሱ ዘንድ ኀይልንና ሥልጣንን ሰጣቸው።

[2] የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩ፥ ድውያንንና ሕሙማንንም ሁሉ እንዲፈውሱ ላካቸው።

[3] እንዲህም አላቸው ፥ “በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ወርቅም ቢሆን፥ ሁለት ልብስም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ።

[4] በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ፤ እስክትሄዱም ድረስ ከዚያ አትውጡ።

[5] የማይቀበሉአችሁ ቢሆን ግን ከዚያች ከተማ ወጥታችሁ ምስክር ሊሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።”

[6] ወጥተውም በየአውራጃዉ መንደሮች ዞሩ፤ በስፍራውም ሁሉ ወንጌልን ሰበኩ፤ ድውያንንም ፈወሱ።

[7] የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ሁሉ ሰምቶ የሚናገረውን ያጣ ነበር፤ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የሚሉ ነበሩና።

[8] ኤልያስ ተገለጠ የሚሉም ነበሩ፤ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል የሚሉም ነበሩና።

[9] ሄሮድስም ፥ “እኔ የዮሐንስን ራስ አስቈረጥሁ፤ እንግዲህ ስለ እርሱ ሲወራ የምሰማው ይህ ማነው?” አለ፤ ሊያየውም ይሻ ነበር።

[10] ሐዋርያትም በተመለሱ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ለብቻቸው ይዞአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ አለ ምድረ በዳ ወጡ።

[11] ሕዝቡም ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀበላቸው፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም አስተማራቸው፤ ሊፈወሱ የሚሹትንም አዳናቸው።

[12] ቀኑም በመሸ ጊዜ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መጥተው ፥ “ያለንበት ምድረ በዳ ነውና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩ የሚበሉትንም እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት ” አሉት።

[13] እርሱ ግን ፥ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው ” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ልንገዛ ካልሄድን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር ሌላ በዚህ የለንም ” አሉት።

[14] ሰዎቹም አምስት ሺህ ያህሉ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱንም ፥ “አምሳ አምሳውን በየክፍላቸው አስቀምጡአቸው ” አላቸው።

[15] እንዲሁም አደረጉ፤ ሁሉም ተቀመጡ።

[16] አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ተመለከተ፤ ባረከ፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው።

[17] ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ያነሡትም የተረፈው ቐርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞላ።

[18] ከዚህም በኋላ ብቻውን ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ሳሉ ፥ “ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።

[19] እነርሱም መልሰው ፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉህ አሉ፤ ኤልያስ ነው የሚሉህም አሉ፤ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል የሚሉህም አሉ ” አሉት።

[20] እርሱም ፥ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው፤ ጴጥሮስም መልሶ ፥ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ ” አለው።

[21] ይህንም ለማንም እንዳይናገሩ ገሠጻቸውና ከለከላቸው።

[22] “ለሰው ልጅ ብዙ መከራ ያጸኑበት ዘንድ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ይፈትኑት ዘንድ፥ ይገድሉትም ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ አለው ” አላቸው።

[23] ሁሉንም እንዲህ አላቸው ፥ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ይሸከም፤ ዕለት ዕለትም ይከተለኝ።

[24] ሰውነቱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ይጥላታል፤ ስለ እኔ ሰውነቱን የጣለ ግን ያድናታል።

[25] ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱንም ካጣ ምን ይረባዋል?

[26] በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅ በክብሩ፥ በአባቱም ክብር፥ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ ሲመጣ ያፍርበታል።

[27] እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩአት ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”

[28] ከዚህም ነገር በኋላ በስምንተኛው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።

[29] ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆነ፤ እንደ መብረቅም አብለጨለጨ።

[30] እነሆም፥ ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር። እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ።

[31] በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ይደረግ ዘንድ ያለውን ክብሩንና መውጣቱን ተናገሩ፤

[32] ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ፈዝዘው አገኘ፤ በነቁም ጊዜ ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ።

[33] ከዚህም በኋላ ከእርሱ ሲለዩ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስን ፥ “መምህር፥ ሆይ፥ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ሦስት ሰቀላዎችንም እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፥ አንዱንም ለሙሴ፥ አንዱንም ለኤልያስ ” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር።

[34] ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ።

[35] ከደመናውም ውስጥ ፥ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት ” የሚል ቃል መጣ።

[36] ቃሉም ከመጣ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ብቻውን ተገኘ፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ያዩትንና የሰሙትንም በዚያ ጊዜ ለማንም አልተናገሩም።

[37] በሁለተኛውም ቀን ከተራራው ወረዱ፤ ብዙ ሕዝብም ተቀበሉት።

[38] አንድ ሰውም በሕዝቡ መካከል ጮኾ እንዲህ አለው ፥ “መምህር ሆይ፥ እርሱ ለእኔ አንድ ነውና ልጄን ታይልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

[39] እነሆ፥ ጋኔን ሊነጥቀኝ ነው፤ ድንገትም ያስጮኸዋል፤ ጥሎም ያፈራግጠዋል፤ አረፋም ያስደፍቀዋል፤ ቀጥቅጦ በጭንቅ ይተወዋል።

[40] እንዲያወጡትም ደቀ መዛሙርትህን ለመንሁአቸው፤ ነገር ግን ማውጣት ተሳናቸው።”

[41] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፥ “የማታምን ከዳተኛ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው ” አለው።

[42] ሲያመጣውም ጋኔኑ ጣለውና አፈራገጠው፤ ጌታችን ኢየሱስም ያን ክፉ ጋኔን ገሠጸው፤ ልጁንም አዳነው፤ ለአባቱም ሰጠው። ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ አደነቁ።

[43] እነርሱም ጌታችን ኢየሱስ ባደረገው ተአምራት ሁሉ ሲደነቁ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው።

[44] “እናንተስ ይህን ነገር በልባችሁ አኑሩት፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለውና።”

[45] እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉትም፤ እንዳይመረምሩት ከእነርሱ የተሰወረ ነውና፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ይፈሩት ነበርና።

[46] እርስ በርሳቸውም ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ ዐሰቡ።

[47] ጌታችን ኢየሱስም በልቡናቸው የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና አንድ ሕፃን ወስዶ በመካከላቸው አቆመው።

[48] እንዲህም አላቸው ፥ “በስሜ እንደዚህ ያለውን ሕፃን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፤ ራሱን ከሁሉ ዝቅ የሚያደርግ እርሱ ታላቅ ይሆናል።”

[49] ዮሐንስም መልሶ ፥ “መምህር ሆይ፥ በስምህ ጋኔን ሲያወጣ ያየነው አንድ ሰው አለ፤ ከእኛም ጋር አልተከተለህምና ከለከልነው፤” አለው።

[50] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “አትከልክሉት፤ ባለጋራችሁ ካልሆነ ባልንጀራችሁ ነውና ” አላቸው።

[51] የመውጣቱ ወራትም በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና።

[52] በፊቱም መልእክተኟችን ላከ፤ ሄደውም ያዘጋጁለት ዘንድ ወደ ሰማርያ ከተማ ገቡ።

[53] ነገር ግን አልተቀበሉትም፤ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቶ ነበርና።

[54] ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስም ይህን ባዩ ጊዜ ፥ “አቤቱ፥ ኤልያስ እንደ አደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንድንል ትፈቅዳለህን?” አሉት።

[55] እርሱ ግን ዘወር ብሎ ፥ “ከምን መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም ” ብሎ ገሠጻቸው።

[56] የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም። ወደ ሌላም መንደር ሄዱ።

[57] ከዚህ በኋላ በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው ፥ “መምህር፥ ወደምትሄድበት ልከተልህን?” አለው።

[58] ጌታችን ኢየሱስም “ለቀበሮዎች ጕuድጓድ አላቸው፤ ለሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም ” አለው።

[59] ሌላውንም ፥ “ተከተለኝ ” አለው፤ እርሱ ግን ፥ “አቤቱ፥ በፊት ሄጄ አባቴን እንድቀብረው ፍቀድልኝ ” አለው።

[60] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዉአቸው፤ አንተ ግን ሂድና የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ ” አለው።

[61] ሦስተኛውም ፥ “አቤቱ፥ ልከተልህን? ነገር ግን ሄጄ ቤተ ሰቦቼን ሁሉ እንድሰናበት ፍቀድልኝ ” አለው።

[62] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ማንም ዕርፍ ይዞ እያረሰ ወደ ኋላው የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይሆንም ” አለው።

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters