[1] ከዚህም በኋላ በአንዲት ቦታ ጸለየ፤ ጸሎቱን በጨረሰ ጊዜም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ፥ “ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ አስተማራቸው ጸሎት አስተምረን ” አለው።
[2] እርሱም እንዲህ አላቸው ፥ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ ፥ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን።
[3] የዕለት ምግባችንን በየዕለቱ ስጠን።
[4] እኛም የበደለንን ሁሉ ይቅር እንድንል በደላችንን ይቅር በለን፤ አቤቱ፥ ወደ ፈተና አታግባን፤ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ።”
[5] እንዲህም አላቸው ፥ “ከመካከላችሁ ወዳጅ ያለው ሰው ቢኖር በመንፈቀ ሌሊትም ወደ እርሱ ሄዶ እንዲህ ቢለው ፥ ‘ወዳጄ ሆይ ሦስት እንጀራ አበድረኝ።
[6] ወዳጄ ከመንገድ መጥቶብኛልና የማቀርብለት የለኝም።’
[7] ያ ወዳጁም ከውስጥ ሆኖ ፥ ‘አትዘብዝበኝ፤ ደጁን አጥብቀን ዘግተናል፤ ልጆችም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል፤ እሰጥህ ዘንድ መነሣት አልችልም ’ ይለዋልን?
[8] ወዳጁ ስለሆነ ሊሰጠው ባይነሣ እንኳ እንዳይዘበዝበው ተነሥቶ የወደደውን ያህል ይሰጠዋል።
[9] እኔም እላችኋለሁ ፥ ለምኑ፥ ይሰጣችኋልም፤ ፈልጉ፥ ታገኛላችሁም፤ ደጅ ምቱ፥ ይከፈትላችኋልም።
[10] የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤ የሚፈልግም ያገኛልና፤ ደጅ ለሚመታም ይከፈትለታልና።
[11] ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ የሚለምነው አባት ቢኖር ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ቢለምነውስ በዓሣ ፋንታ እባብን ይሰጠዋልን?
[12] ወይስ ዕንቐላል ቢለምነው በዕንቐላል ፋንታ ጊንጥ ይሰጠዋልን?
[13] እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠትን የምታውቁ ከሆነ፥ የሰማይ አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካሙን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንዴት አብዝቶ ይሰጣቸው ይሆን?”
[14] ዲዳና ደንቆሮ ጋኔንንም ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ዲዳና ደንቆሮ የነበረው ተናገረ፤ ሰዎችም አደነቁ።
[15] ነገር ግን ከመካከላቸው ፥ “በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣቸዋል ” ያሉ ነበሩ፤ እርሱም መልሶ ፥ “ሰይጣን ሰይጣንን ማውጣት እንደምን ይቻለዋል?” አላቸው።
[16] ሌሎችም ሊፈትኑት ከእርሱ ዘንድ ከሰማይ ምልክትን ይፈልጉ ነበር።
[17] እርሱ ግን የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው ፥ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም እርስ በርሱ ቢለያይ ያ ቤት ይወድቃል።
[18] ሰይጣንስ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል ትላላችሁና።
[19] እኔ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆነ፥ ልጆቻችሁ በምን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ይፋረዱአችኋል።
[20] እኔ በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆነ እንግዲህ አሁን የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።
[21] ኀይለኛ ሰው በጦር መሣሪያ ቤቱን የጠበቀ እንደ ሆነ ገንዘቡ ሁሉ ደኅና ይሆናል።
[22] ከእርሱ የሚበረታው ቢመጣና ቢያሸንፈው ግን፥ ይታመንበት የነበረውን የጦር መሣሪያውን ይገፈዋል፤ የማረከውንና የዘረፈውን ገንዘቡንም ይወስዳል።
[23] ከእኔ ጋር ያልሆነ ባለጋራዬ ነው፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ይበትንብኛል።
[24] “ክፉ ጋኔንም ከሰው በወጣ ጊዜ ውኃ ወደሌለበት ምድረ በዳ ይሄዳል፤ የሚያርፍበትንም መኖሪያ ይሻል፤ ያላገኘ እንደ ሆነም ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል።
[25] በመጣም ጊዜ ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል።
[26] ከዚህም በኋላ ይሄድና ከእርሱ የሚከፉ ሌሎች ባልንጀሮቹን ሰባት አጋንንት ያመጣል፤ ገብተውም በዚያ ሰው ያድሩበታል፤ ለዚያ ሰውም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው የከፋ ይሆንበታል።”
[27] ከዚህም በኋላ ይህን ሲናገር ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን አሰምታ ፥ “የተሸከመችህ ማኅፀን ብፅዕት ናት፤ የጠባሃቸው ጡቶችም ብፁዓት ናቸው ” አለችው።
[28] እርሱም ፥ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁ ናቸው ” አላት።
[29] ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው ሳሉ እንዲህ ይላቸው ጀመረ ፥ “ይቺ ትውልድ ክፉ ናት፤ ምልክትም ትሻለች፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጣትም።
[30] ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው የሰው ልጅም ለዚች ትውልድ እንዲሁ ምልክት ይሆናታል።
[31] የአዜብ ንግሥት በፍርድ ቀን ከዚች ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፋረዳቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ልትሰማ ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ።
[32] የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚች ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፋረዱአታል፤ ያሳፍሩአታልም፤ ዮናስ በሰበከላቸው ጊዜ ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፥ ከዮናስ የሚበልጥ በዚህ አለ።
[33] “በስውር ቦታ ወይም ከዕንቅብ በታች ሊያኖራት መብራትን የሚያበራ የለም፤ የሚመላለሱ ሁሉ ብርሃንን ያዩ ዘንድ በመቅረዝዋ ላይ ያኖራታል እንጂ።
[34] የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ብሩህ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ነው፤ ዐይንህ ታማሚ ቢሆን ግን፤ ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ነው።
[35] እንግዲህ ብርሃንህ ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ።
[36] ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ከሆነ በአንተም ላይ ምንም ጨለማ ባይኖርብህ የመብረቅ ብርሃን እንደሚያበራልህ ሁለንተናህ ብሩህ ይሆናል።”
[37] ይህንም ሲነግራቸው አንድ ፈሪሳዊ በእርሱ ዘንድ ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ገብቶም ለምሳ ተቀመጠ።
[38] ፈሪሳዊዉም አይቶ አደነቀ፤ ምሳ ለመብላት እጁን አልታጠበም ነበርና።
[39] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “እናንተ ፈሪሳውያን፥ ዛሬ የጿውንና የወጭቱን ውጭውን ታጥቡታላችሁ፤ ታጠሩታላችሁም፤ ውስጡ ግን ቅሚያንና ክፋትን የተመላ ነው።
[40] እናንተ ሰነፎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡንስ የፈጠረ አይደለምን?
[41] ነገር ግን የሚወደደውን ምጿት አድርጋችሁ ስጡ፤ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል።
[42] የእንስላልና የጤና አዳም፥ ከአትክልትም ሁሉ ዐስራት የምታገቡ ፍርድንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ቸል የምትሉ እናንተ ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ! ይህንም ልታደርጉ ይገባችኋል፥ ያንም አትተዉ።
[43] እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ! በምኵuራብ ፊት ለፊት መቀመጥን፥ በገበያም እጅ መነሣትን ትወዳላችሁና።
[44] እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ! ሰዎች ሳያውቁ በላዩ እንደሚመላለሱበት እንደ ተሰወረ መቃብር ናችሁና።”
[45] ከሕግ ዐዋቂዎችም አንዱ መልሶ ፥ “መምህር ሆይ፥ ይህን ስትል እኛን እኮ መስደብህ ነው ” አለው።
[46] እርሱም እንዲህ አለው፤ “ለእናንተ ለሕግ ዐዋቂዎች ወዮላችሁ! ሰውን ከባድ ሸክም ታሸክሙታላችሁ፤ እናንተ ግን ያን ሸክም በአንዲት ጣታችሁ እንኳን አትነኩትም።
[47] እናንተ ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ! አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁና።
[48] የአባቶቻችሁም ሥራ ደስ አሰኝቶአችኋል፤ የምትመሰክሩባቸውም እናንተ ራሳችሁ ናችሁ፤ እነርሱ የገደሉአቸውን መቃብራቸውን እናንተ ትሠራላችሁና።
[49] ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥበቡ እንዲህ አለች ፥ እነሆ፥ እኔ ነቢያትንና ሐዋርያትን ወደ እነርሱ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ይገድላሉ፤ ያሳድዳሉም።
[50] ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚህች ትውልድ ድረስ ስለ ፈሰሰው ስለ ነቢያት ሁሉ ደም ይበቀላቸው ዘንድ፥
[51] ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ገደሉት እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ እውነት እላችኋለሁ ከዚች ትውልድ ይፈለጋል።
[52] እናንተ ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ወዮላችሁ! የጽድቅንና የዕውቀትን መክፈቻ ወስዳችሁ ትሰውራላችሁና፤ እናንተም አትገቡምና፤ የሚገቡትንም መግባትን ትከለክሉአቸዋላችሁ።”
[53] በሕዝቡም ሁሉ ፊት ይህን ሲነግራቸው ጻፎችና ፈሪሳውያን አጽንተው ይጣሉት፥ ይቀየሙትም ጀመር።
[54] በአነጋገሩም ሊያስቱትና ሊያጣሉት ያደቡበት ነበር።