[1] በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቈጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ።
[2] ቄሬኔዎስ ለሶርያ መስፍን በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመርያ ቈጠራ ሆነ።
[3] ሰው ሁሉ ሊቈጠር ወደየከተማው ሄደ።
[4] ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ቤተ ልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱ ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹም ወገን ነበርና።
[5] ፀንሳ ሳለች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ሄደ።
[6] በዚያ ሳሉም የምትወልድበት ቀን ደረሰ።
[7] የበኵuር ልጅዋንም ወለደች፤ አውራ ጣቱንም አሰረችው፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በበረትም አስተኛችው፤ በማደርያቸው ቦታ አልነበራቸውምና።
[8] በዚያ ሀገር እረኟች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር።
[9] እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሀትንም ፈሩ።
[10] መልአኩም እንዲህ አላቸው ፥ “እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ።
[11] እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።
[12] ለእናንተም ምልክቱ እንዲህ ነው ፥ ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፥ በጨርቅም ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኛላቸሁ።”
[13] ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ።
[14] “ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፥ ሰላምም በምድር፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ” ይሉ ነበር።
[15] ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በዐረጉ ጊዜ እነዚያ እረኟች ሰዎች እርስ በርሳቸው ፥ “እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ ” አሉ።
[16] ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፤ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝቶ አገኙት።
[17] በአዩም ጊዜ የነገሩአቸው ስለዚህ ሕፃን እንደ ሆነ ዐውቀው አወሩ።
[18] የሰሙትም ሁሉ እረኟቹ የነገሩአቸውን አደነቁ።
[19] ማርያም ግን ይህን ሁሉ ትጠብቀው፥ በልብዋም ታኖረው ነበር።
[20] እረኟችም እንደ ነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።
[21] ስምንት ቀን በተፈጸመ ጊዜም ሕፃኑን ሊገዝሩት ወሰዱት፤ በማኅፀንዋ ሳትፀንሰው መልአኩ እንዳወጣለትም ስሙን ኢየሱስ አሉት።
[22] የመንጻታቸውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ እንደ ሙሴ ሕግ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሙት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት።
[23] “በኵuር ሆኖ የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይባላል ” ተብሎ በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈ፥
[24] በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ታዘዘ ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ስለ እርሱ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡለት ዘንድ።
[25] በኢየሩሳሌምም ስሙ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ጻድቅና ደግ ሰው ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን ደስታቸውን ያይ ዘንድ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ነበር።
[26] የእግዚአብሔርንም መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር።
[27] መንፈስም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደው፤ ዘመዶቹም በሕግ የተጻፈውን ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ጌታችን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ በአገቡት ጊዜ፥
[28] እርሱ ደግሞ ተቀብሎ በክንዱ ታቀፈው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው።
[29] እንዲህም አለ፤ “አቤቱ፥ እንደ አዘዝህ ዛሬ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ።
[30] ዐይኖቼ ትድግናህን አይተዋልና።
[31] በወገንህ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፥
[32] ለአሕዛብ ብርሃንን፥ ለወገንህ ለእስራኤልም ክብርን ትገልጥ ዘንድ።”
[33] ዮሴፍና እናቱ ግን በእርሱ ላይ ስለሚናገረው ያደንቁ ነበር።
[34] ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው፤
[35] ባንቺ ግን በልብሽ ፍላጻ ይገባል፤ የብዙዎቹን ዐሳብ ይገልጥ ዘንድ።”
[36] ከአሴር ወገን የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል ነቢይት ነበረች፤ አርጅታም ነበር፤ ከድንግልናዋም በኋላ ከባል ጋር ሰባት ዓመት ኖረች።
[37] ሰማንያ አራት ዓመትም መበለት ሆና ኖረች፤ በጿምና በጸሎትም እያገለገለች፥ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አትወጣም ነበር።
[38] ያንጊዜም ተነሥታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ድኅነት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለ እርሱ ተናገረች።
[39] በእግዚአብሔርም ሕግ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ።
[40] ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ጥበብንም የተመላ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረች።
[41] ዘመዶቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።
[42] ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንደ አስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ።
[43] ሥራቸውንም ጨርሰው ተመለሱ፤ ሕፃኑ ጌታችን ኢየሱስ ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ ዮሴፍና እናቱም አላወቁም ነበር።
[44] በመንገድም ከሰዎች ጋር ያለ መስሎአቸው ነበር፤ ያንድ ቀን መንገድንም ከሄዱ በኋላ ዕለቱን ከዘመዶቹ፥ ከሚያውቁትም ዘንድ ፈለጉት።
[45] ባላገኙትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
[46] ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ቀን በቤተ መቅደስ በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት።
[47] የሰሙትም ሁሉ አስተዋይነቱንና አመላለሱን ያደንቁ ነበር።
[48] በአዩትም ጊዜ ደነገጡ፤ እናቱም ፥ “ልጄ፥ ለምን እንዲህ አደረግኸን? እነሆ አባትህም፥ እኔም ስንፈልግህ ደከምን ” አለችው።
[49] እርሱም ፥ “ለምን ትፈልጉኛላችሁ? በአባቴ ቤት ልኖር እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው።
[50] እነርሱ ግን የነገራቸውን ቃል አላስተዋሉም።
[51] ከእነርሱም ጋር ሂዶ ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር፤ እናቱ ግን ይህን ሁሉ ነገር ትጠብቀው፥ በልብዋም ታኖረው ነበር።
[52] ጌታችን ኢየሱስም በእግዚአብሔር ዘንድ፥ በሰውም ዘንድ፥ በጥበብና በአካል በሞገስም አደገ።