Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:32

[1] ከዚህም በኋላ ሄዶ ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት በሰንበት ቀን እህል ሊበላ ገባ፤ እነርሱ ግን ይጠባበቁት ነበር።

[2] እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ አንድ ሰው በፊቱ ነበር።

[3] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን ፥ “በሰንበት ድውይ መፈወስ ይገባልን? ወይስ አይገባም?” ብሎ ጠየቃቸው።

[4] እነርሱም ዝም አሉ፤ ይዞም ፈወሰውና ሰደደው።

[5] “ከእናንተ በሬው ወይም አህያው በጕuድጓድ ውስጥ የወደቀበት አንድ ሰው ቢኖር ዕለቱን በሰንበት ቀን ያነሣው የለምን?” አላቸው።

[6] ስለዚህም ነገር ሊመልሱለት አልተቻላቸውም።

[7] በምሳ ላይ ለነበሩትም ወደ ላይኛው ወንበር ሲሽቀዳደሙ ባያቸው ጊዜ ምሳሌ መስሎ አስተማራቸው።

[8] እንዲህም አለ ፥ “ለምሳ የጠራህ ሰው ቢኖርና ብትሄድ በላይኛው መቀመጫ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ የሚበልጥ ይመጣ ይሆናል።

[9] በኋላ ያ አንተንም እርሱንም የጠራ መጥቶ ፥ ይህን ቦታ ለእርሱ ተውለት ይልሃልና፤ ያንጊዜም አፍረህ ትመለሳለህ፤ ወደ ዝቅተኛ ቦታም ትወርዳለህ።

[10] የጠራህ ሰው ቢኖርና ብትሄድ ግን የጠራህ በመጣ ጊዜ ወዳጄ ወደ ላይኛው መቀመጫ ውጣ ይልህ ዘንድ በታችኛው መቀመጫ ተቀመጥ፤ ያንጊዜም ከአንተ ጋር ለማዕድ በተቀመጡት ሰዎች ፊት ክብር ይሆንልሃል።

[11] ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ያሚያዋርድ ከፍ ይላልና።”

[12] የጠራውንም እንዲህ አለው ፥ “በበዓል ምሳ ወይም ራት በምታደርግበት ጊዜ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፥ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፥ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና።

[13] ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፥ ዕውሮችን፥ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ።

[14] አንተም ብፁዕ ትሆናለህ፤ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ።”

[15] ለምሳ ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ ፥ “በእግዚአብሔር መንግሥት እህል የሚበላ ብፁዕ ነው ” አለው።

[16] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “አንድ ሰው ታላቅ ምሳ አደረገና ብዙ ሰዎችን ጠራ።

[17] ለምሳ የተጠሩበትም ቀን በደረሰ ጊዜ የታደሙትን ይጠራቸው ዘንድ አገልጋዩን ላከ፤ እርሱም ሄዶ የታደሙትን ፥ አሁን ምሳውን ፈጽመን አዘጋጅተናልና ኑ አላቸው።

[18] ሁሉም በአንድ ቃል ተባብረው እንቢ አሉ፤ የመጀመሪያው ፥ እርሻ ገዝቼአለሁ፤ ሄጄም ላያት እሻለሁ፤ እንቢ እንደ አላልሁ ቐጠርልኝ በለው አለው።

[19] ሁለተኛውም ፥ አምስት ጥማድ በሬ ገዝቻለሁ፤ ላያቸውና ልፈትናቸው እሄዳለሁ፤ እንደ መጣሁ፥ እንቢ እንደ አላልሁም ቐጠርልኝ በለው አለው።

[20] ሦስተኛውም ፥ ሚስት አግብቼአለሁ፤ ስለዚህ ልመጣ አልችልም በለው አለው።

[21] አገልጋዩም ተመልሶ ለጌታው ይህንኑ ነገረው፤ ያንጊዜም ባለቤቱ ተቈጣ፤ አገልጋዩንም ፥ ፈጥነህ ወደ አደባባይና ወደ ከተማው ጐዳና ሂድ፤ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፥ ዕውሮችንና አንካሶችን ወደዚህ አምጣልኝ አለው።

[22] ከዚህም በኋላ አገልጋዩ ፥ አቤቱ እንደ አዘዝኸኝ አደረግሁ፤ ገናም ቦታ አለ አለው።

[23] ጌታውም አገልጋዩን ፥ ወደ መንገዶችና ወደ ከተማው ቅጥር ፈጥነህ ሂድና ቤቴ እንዲመላ ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው አለው።

[24] ከእነዚህ ከታደሙት ሰዎች አንዱ ስንኳን ማዕዴን እንደማይቀምሳት እነግራችኋለሁ።”

[25] ከዚህም በኋላ ብዙ ሰዎች አብረውት ሲሄዱ መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው።

[26] “ወደ እኔ የሚመጣ፥ ሊከተለኝም የሚወድ አባቱንና እናቱን፥ ሚስቱንና ልጆቹን፥ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፥ የራሱንም ሰውነት እንኳ ቢሆን የማይጠላ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።

[27] መስቀሉን ተሸክሞ ሊከተለኝ የማይመጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።”

[28] “ከእናንተም ወገን የግንብ ቤት መሥራት የሚወድ ቢኖር ይጨርሰው ዘንድ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የሚፈጅበትን የማያስብ ማን ነው?

[29] መሠረቱን ጥሎ መጨረስ ያቃተውም እንደ ሆነ ያዩት ሁሉ፥

[30] ‘ይህ ሰው ሊሠራ ጀመረ፤ ግን መጨረስ ተሳነው ’ እያሉ ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።

[31] ንጉሥም ሌላውን ንጉሥ ይወጋ ዘንድ ሊሄድ ቢወድ ሁለት እልፍ ይዞ ወደ እርሱ የሚመጣውን በአንድ እልፍ ሊዋጋው ይችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ይመክር የለምን?

[32] ያለዚያ ግን፥ ገና በሩቁ ሳለ አማላጆች መልእክተኟችን ልኮ ዕርቅ ይለምናል።

[33] እንግዲህ እንደዚሁ ከእናንተ ወገን ከሁሉ ያልወጣ፥ የእርሱ ገንዘብ ከሆነውም ሁሉ ያልተለየ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።

[34] “ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ከሆነ እንግዲህ በምን ያጣፍጡታል?

[35] ለምድርም ቢሆን፥ ለፍግ መቆለያም ቢሆን አይረባም፤ ነገር ግን ወደ ውጭ ይጥሉታል፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters