Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 6:43

[1] ከዚህም በኋላ በአንድ ቀን ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምራቸው፥ ወንጌልንም ሲነግራቸው፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ተነሡበት።

[2] “ይህን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ እንድታደርግ ማን ፈቀደልህ? እስኪ ንገረን ” አሉት።

[3] እርሱም መልሶ ፥ “እኔም አንዲት ነገርን እጠይቃችኋለሁ፤ ንገሩኝ፤

[4] የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ናት? ከሰማይ ናትን? ወይስ ከሰው?” አላቸው።

[5] እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፤ “ከሰማይ ነው ብንለው ለምን አላመናችሁትም? ይለናል።

[6] ከሰው ነው ብንለውም ሕዝቡ ሁሉ በድንጋይ ይወግሩናል፤ ሁሉም ዮሐንስ ነቢይ እንደ ሆነ አምነውበታልና።

[7] ከወዴት እንደ ሆነች አናውቅም ” ብለው መለሱለት።

[8] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “እኔም ይህን በማን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም ” አላቸው።

[9] ለሕዝቡም ይህን ምሳሌ ይመስልላቸው ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው ፥ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ መጭመቂያም አስቈፈረ፤ ግንብም ሠራለት፤ ለገባሮችም ሰጥቶ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ ሳይመለስም ዘገየ።

[10] የመከሩ ወራት በሆነ ጊዜም ወደ ገባሮቹ፥ ከወይኑ ፍሬ ይልኩለት ዘንድ አገልጋዩን ላከ፤ ገባሮቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት።

[11] ዳግመኛም ሌላውን አገልጋዩን ላከ፤ እርሱንም ደብድበውና አዋርደው ባዶ እጁን ሰደዱት።

[12] ደግሞ ሦስተኛውን አገልጋዩን ላከ፤ እርሱንም አቐስለው ሰደዱት።

[13] የወይኑ ባለቤትም ፥ እንግዲህ ምን ላድርግ? ምናልባት እርሱን እንኳ አይተው ያፍሩ እንደ ሆነ የምወደውን ልጄን ልላክ ብሎ ላከው።

[14] ገባሮቹም ባዩት ጊዜ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እንውሰድ ብለው ተማከሩ።

[15] ከወይኑ ቦታም ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት።

[16] የወይኑ ባለቤት በመጣ ጊዜ እንግዲህ ምን ያደርጋቸዋል? ይመጣል፤ እነዚያንም ገባሮች ይገድላቸዋል፤ ወይኑንም ለሌሎች ገባሮች ይሰጣል፤” ቃሉንም ሰምተው ፥ “አይሆንም፤ እንዲህ አይደረግም ” አሉ።

[17] ጌታችን ኢየሱስም ተመለከተና እንዲህ አላቸው፤ “ግንበኟች የናቁአት ድንጋይ እርስዋ የማዕዘን ራስ ሆነች፥ የሚለው ጽሑፍ ምንድነው?

[18] በዚያች ድንጋይ ላይ የወደቀ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ እርስዋም የወደቀችበትን ታደቅቀዋለች።”

[19] ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ሊይዙት ወደዱ፤ ይህን ስለ እነርሱ እንደ መሰለ ዐውቀዋልና፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩአቸው።

[20] ከእነርሱም ተለይተው ከሄዱ በኋላ፥ የሚጠባበቁትን አዘጋጁለት፤ በአነጋገሩም ያስቱት ዘንድ ወደ መኳንንትና ወደ መሳፍንት አሳልፈው ሊሰጡት ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰላዮችን ወደ እርሱ ላኩ።

[21] እነርሱም እንዲህ ብለው ጠየቁት ፥ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነት እንደምትናገርና እንደምታስተምር፥ ፊት አይተህም እንደማታዳላ፥ የእግዚአብሔርንም መንገድ በቀጥታ እንደምታስተምር እናውቃለን።

[22] ለቄሣር ግብር መስጠት ይገባል? ወይስ አይገባም?”

[23] ተንኰላቸውንም ዐውቆ ፥ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? ገንዘቡን አሳዩኝ ” አላቸው።

[24] አምጥተውም አሳዩት፤ “መልኩ፥ ጽሕፈቱስ የማነው?” አላቸው፤ እነርሱም ፥ “የቄሣር ነው ” ብለው መለሱለት።

[25] እርሱም ፥ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ ” አላቸው።

[26] በሕዝቡም ሁሉ ፊት በአነጋገሩ ማሳሳት ተሳናቸው፤ መልሱንም አድንቀው ዝም አሉ።

[27] “ሙታን አይነሡም ” ከሚሉ ከሰዱቃውያንም አንዳንድ ሰዎች ወደ እርሱ መጡ።

[28] እነርሱም እንዲህ ብለው ጠየቁት ፥ “መምህር ሆይ፥ ሙሴ ፥ ‘ወንድሙ ልጅ ሳይወልድ ሚስቱን ትቶ የሞተበት ሰው ቢኖር ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ’ ሲል ጽፎልናል።

[29] እንግዲህ ከእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ታላቁ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ።

[30] እንደዚሁም ሁለተኛው አገባት፤ እርሱም ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤

[31] ሦስተኛውም አገባት፤ እንዲሁም ሰባቱ ሁሉ አገቡአት፤ ልጅ ሳይወልዱም ሞቱ።

[32] ከሁሉም በኋላ ያቺ ሴት ሞተች።

[33] እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ከእነርሱ ለማንኛው ሚስት ትሆናለች? ሰባቱም ሁሉ አግብተዋት ነበርና።”

[34] ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፥ ይጋባሉም፤ ይወልዳሉ፥ ይዋለዳሉም።

[35] ያን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ሊወርሱ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም፤ አይጋቡም።

[36] እንግዲህ ወዲህ ሞት የለባቸውም፤ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ናቸው እንጂ፤ የትንሣኤ ልጆችም ስለሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ።

[37] ሙታን እንደሚነሡስ እግዚአብሔር ፥ ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ’ ብሎ በቐጥቌጦው ዘንድ እንደ አነጋገረው ሙሴ ተናግሮአል።

[38] እንኪያስ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ሁሉም በእርሱ ዘንድ ሕያዋን ናቸውና።”

[39] ከጻፎችም ወገን የሆኑ ሰዎች ፥ “መምህር ሆይ፥ መልካም ብለሃል ” ብለው መለሱ።

[40] ከዚያ ወዲህ ግን ሊጠይቀው የደፈረ ማንም የለም።

[41] እንዲህም አላቸው ፥ “ክርስቶስን እንዴት የዳዊት ልጅ ይሉታል?

[42] እርሱ ራሱ ዳዊት በመዝሙር መጽሐፍ ‘ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፥

[43] ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስከ አደርጋቸው ድረስ ’ ብሏል።

[44] እንግዲህ እርሱ ራሱ ዳዊት ‘ጌታዬ ’ ያለው እንዴት ልጁ ይሆናል?”

[45] ሕዝቡም ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው።

[46] “ልብሳቸውን አንዘርፍፈው ወዲያ ወዲህ ማለትን ከሚሹ፥ በገበያ እጅ መነሣትንና በአደባባይ ፊት ለፊት፥ በማዕድም ጊዜ በከበሬታ መቀመጫ መቀመጥን ከሚወዱ ጻፎች ተጠበቁ።

[47] የመበለቶችን ገንዘብ የሚበሉ፥ ለምክንያት ጸሎትንም የሚያስረዝሙ እነዚህ ታላቅ ፍርድን ይቀበላሉ።”

የሉቃስ ወንጌል። — Chapters